የቅባት እህሎች እና የጥራጥሬ ምርቶች የቀጥታ ግብይት መመሪያ ጸደቀ

ጥቅምት 4/2017 (አዲስ ዋልታ) የቅባት እህሎች እና የጥራጥሬ ምርቶች የቀጥታ ግብይት መመሪያ ቁጥር 1026/2017 መጽደቁን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) አስታወቁ።

ሚኒስትሩ እንዳሉት በ2017 ዓ.ም የጥራጥሬ እና ቅባት እህሎች የወጪ ንግድ አፈፃፀም በማሻሻል ከንዑስ ዘርፉ የወጪ ንግድ ከ750 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለማስገኘት ሰፊ ርብርብ በመደረግ ላይ ይገኛል::

ይህንን ጥረት ሊያግዝ የሚያስችል የቅባት እህሎች እና የጥራጥሬ ምርቶች የቀጥታ ግብይት መመሪያ ቁጥር 1026/2017 ማጽደቃቸውን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል::

መመሪያው በዘርፉ ይስተዋሉ የነበሩ የግብይት ማነቆዎችን ከመፍታት ባሻገር ወጪን በመቀነስ፣ ተደራሽነትን በማሻሻል እና የግብይት ሰንሰለቱን በማሳጠር የወጪ ንግድ ተወዳዳሪነትን ያረጋግጣል ብለዋል::

ላኪዎች ምቹ ሁኔታውን በመጠቀም ምርት እንድትገዙና እንድትልኩ ጥሪ አቅርበዋል::