የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሞሮኒ አዲስ በረራ ሊጀምር ነው

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኮሞሮስ ዋና ከተማ ሞሮኒ አዲስ በረራ ሊጀምር መሆኑን አስታወቀ።

የመጀመሪያ በረራውን በቦይንግ /B737-800/ አውሮፕላን በጥቅምት ወር 2009 ዓ.ም እንደሚያደርግም ይጠበቃል።

የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማሪያም አየር መንገዱ ወደ ወደብ ከተማዋ ሞሮኒ በረራውን ለመጀመር በዝግጅት ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

የአፍሪካን አህጉራዊ ትስስርና እድገት በማፋጠን በተለይም ለኢንቨሰትመንት፣ንግድና ቱሪዝም እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

በቀጣይም ወደ ኮሞሮስ ደሴቶች መዳረሻውን የማስፋት እቅድ እንዳለውም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከአፍሪካ ከተሞች በኬፕታውን፣ጋቦሮኒ እንዲሁም ጎማ የጀመራቸውን አዳዲስ በረራዎች ጨምሮ መዳረሻውን ማስፋቱ ይታወሳል። 

በቀጣይ ወደ ሞሮኒ የሚደረገው በረራ ሲጨመር የአፍሪካ መዳረሻውን 54 ያደርሰዋል።

አየር መንገዱ በዓለም አምስት አህጉሮች 93 መዳረሻዎች አሉት።( ኢዜአ)