የአዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም በግማሽ ዓመቱ ከ880 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር ለተጠቃሚዎች መሥጠቱን አስታወቀ ።
የተቋሙ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ መስፍን ፊጡማ ዋልታ እንደገለጹት ባለፉት ስድስት ወራት ተቋሙ ለ 23ሺ 690 የሚሆኑ ተበዳሪዎች 1 ቢሊዮን 92 ሚሊዮን 229 ሺ ብር ብድር ለመሥጠት አቅዶ በአጠቃላይ ለ 13ሺ 968 ተበዳሪዎች 880 ሚሊዮን 391 ሺ ብር ብድር መሥጠት ተችሏል ።
በሩብ ዓመቱ ከተቋሙ ብድር የወሰዱት በማኑፋክቸሪንግ ፣በኮንስትራክሽን ፣ በአገልግሎት፣ በንግድ፣ በከተማ ግብርና በትራንስፖርት ዘርፎች የተሠማሩ ነዋሪዎች መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ መስፍን በአገልግሎትና በንግድ ዘርፍ የተሠማሩት ዜጎች ከፍተኛውን ብድር መጠን ማግኘት ችለዋል ብለዋል ።
ተቋሙ በአዲስ አባባ ከተማና አካባቢዋ የሚገኙ ሥራ አጥ ወጣቶችና ሴቶችን የብድር ድጋፍ በማቅረብ የበኩሉን አስተዋጽኦ እያደረገ ነው ያሉት አቶ መስፍን በግማሽ ዓመቱ ሴቶች 46 በመቶ ወጣቶች 36 በመቶ የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ ሆነዋል ።
በተጨማሪም በግማሽ ዓመቱ 760 ሚሊዮን ብር ከደንበኞች በቁጠባ መልኩ ለመሰብሰብ ያቀደው ተቋሙ በአጠቃላይ 791 ሚሊዮን ብር ወይም የዕቅዱን 103 ነጥብ5 በመቶ መሰብሰብ መቻሉን አቶ መስፍን አያይዘው ገልጸዋል ።
አዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም በ1993 ዓም የተቋቋመ ሲሆን ከ4 ቢሊዮን ብር በላይ የተከፈለ ካፒታል እያንቀሳቀሰ ይገኛል ።