ባለሥልጣኑ በግማሽ ዓመቱ 71 ነጥብ1 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በግማሽ ዓመቱ የሥራ አፈጻጸም 71 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ ።

በባለሥልጣኑ የትምህርትና ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ኤፍሬም መኮንን ለዋልታ እንደገለጹት ባለሥልጣኑ ባለፉት ስድስት ወራት በአጠቃላይ 82 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ 71 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ ተችሏል ።

ባለሥልጣኑ በግማሽ ዓመቱ ገቢውን የሰበሰበው ከአገር ውስጥ ግብር ፣ ከወጪ ንግድ ቀረጥና ግብር እንዲሁም ከብሔራዊ ሎተሪ መሆኑን አቶ አፍሬም ተናግረዋል ።

በአጠቃላይ ከግብርና ከቀረጥ የተገኘው ገቢ ከዓምና ጋር ሲነጻጻር የ11 በመቶ እንዳለውም አቶ ኤፍሬም አያይዘው ገልጸዋል ።

ባለሥልጣኑ የኮንትሮባንድ  ንግድን ለመቆጣጣር በግማሽ ዓመቱ በወሰዳቸው እርምጃዎች በአጠቃላይ  በህገ ወጥ መልኩ ወደ አገር ውስጥ ሲገቡና  ሲወጡ የተያዙ  428 ሚሊዮን ብር  የሚያወጡ የተለያዩ እቃዎች እንዲወረሱ ተደርጓል  ።

የግብር ከፋዩ  ህብረተሰብ  ግብርን መክፈል ግዴታው መሆኑን ተረድቶ የሚጠበቅበትን ክፍያ  እንዲፈጽም  ለማድረግ በግማሽ ዓመቱ የውይይት መድረክና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች  ሲከናወኑ መቆየታቸውን አመልክተዋል ።

የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም  የጣት አሻራ ከግብር ከፋዩ በመውሰድ፣ የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያዎችን በማስፋፋትና የጉምሩክ አገልግሎት  መስጪያ መሣሪያዎችን የማዘመን ሥራዎች መካሄዳቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን  ማዕከል ዘግቧል ።