ሚኒስቴሩ የሐር ምርት ስትራቴጂ እያዘጋጀ መሆኑን አስታወቀ

ሀገራዊ የሐር ምርትን ወደ ላቀ ምዕራፍ ለማሸጋገር የሚያስችል የሐር ምርት ስትራቴጂ እያዘጋጀ መሆኑን የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በሚኒስቴሩ የማርና ሐር ልማት ተወካይ ዳይሬክተር አቶ ደምሰው ዋቅጅራ ከዋልታ  ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ስትራቴጂው ለሐር ልማት ሰፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠርና ከዘርፉ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ 3 ነጥብ 5 ቶን ማምረት እንደተቻለ አቶ ደምሰው አስታውቀዋል ፡፡

ይሁንና  በቅርቡ የሐር ምርት ዋጋ በፊት ከነበረበት በሶስት እጥፍ በመጨመሩ ምክንያት ገዢ በማጣቱ  በክልሎች ምርታማነት ላይ   መቀዛቀዝ ማሳየቱን አስረድተዋል ፡፡

በአማራ፣ ትግራይና ኦሮሚያ ክልሎች እየተመረተ ቢቆይም አሁን ግን በደቡብ ክልል ብቻ ተወስኖ መቅረቱን ዳይሬክተሩ  አመልክተዋል፡፡

በመልካሳ የሐር ምርት ምርምር ጣቢያ 2ሺህ 500 ወጣቶችን  በማሰልጠን ወደ ሥራ በማሰማራት ዘርፉ እንዲያንሰራራ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል ፡፡

የሐር ትል የሚመገበው የእንጆሪና የጉሎ ቅጠል በመሆኑ ስራውን ይበልጥ ቀላል እንሚያደርገውም ገልጸዋል፡፡

ምርቱ በቤተሰብ ደረጃ ጭምር በየ45ቀኑ የሐር ምርት መሰብሰብ ስለሚቻል በጥቂት ጊዜ ውስጥ ውጤታማ የሚያደርግ አዋጪ የሥራ ዘርፍ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ዘርፉ ቢሰራበት በዓለም ገበያ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኝ ከመሆኑም በላይ ለሀገር ውስጥ የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪዎች 1ሺህ ኩንታል ፍላጎት በማሟላት የውጭ ምንዛሬን ማዳን እንደሚቻል አስረድተዋል ፡፡

ስለሆነም የግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር፣ ንግድ ሚኒስቴርና የእንስሳትና ዓሣ ሐብት ሚኒስቴር በጋራ ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት በመስጠት እየሰሩበት እደሆነም ገልጸዋል፡፡

ዘንድሮ ምርቱን ከ6 ነጥብ 7 በላይ ቶን ለማሳደግ መታቀዱን ገልጸዋል ፡፡

ባለፈው የበጀት ዓመት የተመረተው 2 ቶን ብቻ እንደነበረ ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል ፡፡

የሐር ልማት በኢትዮጵያ በርካታ ዓመታትን ቢያስቆጥርም ከአስር ዓመት በፊት ጥሩ እንቅስቃሴ እንደነበረውም ጨምረው አንስተዋል  ፡፡