ኢትዮ-ቴሌኮም በግማሽ ዓመቱ 15 ነጥብ64 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ

ኢትዮ-ቴሌኮም በዘንድሮ የበጀት ዓመት የግማሽ ዓመት ከተለያዩ አገልግሎቶች በአጠቃላይ  15 ነጥብ 64 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ ።

የኢትዮ ቴሌኮም የኮርፖሬት ኮሚኒኬሽን ኦፊሰር አቶ አብዱራሂም አህመድ ለዋልታ እንደገለጹት የኩባንያው ገቢ ካለፈው የበጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጻር  የ17በመቶ  ዕድገት  ተመዝግቧል ።

ኢትዮ-ቴሌኮም በግማሽ ዓመቱ ያልተጣራ ትርፍ መጠን በአጠቃላይ 11 ነጥብ 91 ቢሊዮን መሆኑን  የጠቆሙት አቶ አብዱራሂም የተገኘው የተጣራ ትርፍ ከዓምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጻር  የ18 በመቶ ዕድገት አሳይቷል ብለዋል ።

በአጠቃላይ በግማሽ ዓመቱ ከተለያዩ አገልግሎቶች ከተገኘው ገቢ ውስጥ 74 ነጥብ 5 በመቶ የሚሆነው ከሞባይል አገልገሎት፣ 14 በመቶው ከዳታና ኢንተርኔት እንዲሁም  7 በመቶ ገቢ ከዓለም አቀፍ አገልግሎቶች የተገኘ መሆኑን አቶ አብዱራሂም አስረድተዋል ።

እንደ አቶ አብዲራሂም  ገለጻ  በአሁኑ ወቅት በአጠቃላይ የኢትዮ – ቴሌኮም ደንበኞች ብዛት ከ 52  ሚሊዮን በላይ የደረሰ መሆኑንና ከዚህም ውስጥ 51  ሚሊዮን የሚሆኑት የሞባይል አገልግሎት ተጠቃሚዎች ሲሆኑ 14 ነጥብ 5  ሚሊዮን የሚሆኑት የኢንተርኔትና ዳታ አገልግሎት ተጠቃሚ   ናቸው ።        

ኢትዮ- ቴሌኮም የአገሪቱን የቴሌኮም መሠረተ ልማት ደህንነትን ከማረጋገጥና የቴሌኮም ማጭበርበርን ከመከላከል አንጻር የህብረተሰቡን ግንዛቤ ከማሳደግ ጎን ለጎን በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል ፡፡