በዘንድሮ የበጀት ዓመት ባለፉት ስምንት ወራት ከቆዳ ኢንዱስትሪ ምርቶች ከ70 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ ።
በሚኒስቴሩ የቆዳና ጫማ ዘርፍ ኢንዱስትሪ ክትትልና ድጋፍ ዳይሬክተር አቶ አድማሱ ይፍሩ ለዋልታ እንደገለጹት በዘንድሮ የበጀት ባለፉት ስምንት ወራት የተለያዩ የቆዳ ውጤቶችን ወደ ውጪ በመላክ 70 ሚሊዮን 496 ሺ የአሜሪካን ዶላር ገቢ ተገኝቷል ።
ሚኒስቴሩ የተለያዩ የቆዳ ውጤቶችን ወደ ውጭ በመላክ 149 ሚሊዮን 890ሺ የአሜሪካ ዶላር ለማግኘት መታቀዱን ያስታወሱት አቶ አድማሱ ለገቢው መቀነስ የተለያዩ የቆዳ ፕሮጀክቶች መዘግየታቸውና በዓለም ገበያ የቆዳ ውጤቶች ፍላጎት መቀነስ ዋናነት የሚጠቀሱ ምክያቶች መሆናቸውን ገልጸዋል ።
ወደ ውጭ የተላኩት የቆዳ ውጤቶች ጫማዎች ፣ ያለቀላቸው የቆዳ ውጤቶች፣ የቆዳ ጓንቶችና የቆዳ አልባሳት መሆናቸውን አቶ አድማሱ ተናግረዋል ።
በቆዳው ዘርፍ የባለሙያዎችን አቅም ለማሳደግ የኢትዮጵያ የቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ከህንድ የቆዳ ልማት ድርጅት ጋር በመተባባር ከ60 በላይ የሚሆኑ ባለሙያዎች በህንድ አገር በፒኤች ዲና በማስተርስ ዲግሪ በቆዳ ቴክኖሎጂ እየሠለጠኑ እንደሚገኙ አቶ አድማሱ አስረድተዋል ።
በተጨማሪም በአገር ውስጥ የሚገኙ ነባር የቆዳ ፋብሪካዎች ያለቀለትን የቆዳ ውጤት ወደ ውጭ የመላክ አቅማቸውን ለማሳደግ ከእንግሊዝ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት ጋር በመተባባር ከ10 ፋብሪካዎች ጋር ያለቀለትን የቆዳ ውጤት ለመላክ የተቀናጀ ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አቶ አድማሱ አመልክተዋል።
እንደ አቶ አድማሱ ገለጻ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በቆዳው ዘርፍ ያለውን ዕምቅ ሃብት ለመጠቀም የቻይናው ሁጁዋን ፣ የታይዋኑን ጆርጅ ሹና ከአገር ውስጥ የአንበሳ የቆዳና ጫማ ፋብሪካዎችን በስፋት ወደ ምርት እንዲገቡ እንቅስቃሴ ተጀምሯል ።
የግንባታ ፕሮጀክቶቻቸው ያላለቁት የቆዳ ፋብሪካዎች በሙሉ አቅማቸው ሥራ ሲጀምሩ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ወደ ሥራ ያስገባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አቶ አድማሱ አስረድተዋል ።
ኢትዮጵያ ከ2003 ዓም ጀምሮ ጥሬ ቆዳን ወደ ውጭ መላክ ያቆመች ሲሆን እሴት የተጨመሩባቸውን የቆዳ ውጤቶች ወደ የተለያዩ አገራት እየላከች መሆኑን ዋሚኮ ዘግቧል ።