በዓመት 1 ነጥብ 4 ሚሊየን ቶን የማምረት አቅም ያለው ሐበሻ ሲሚንቶ ፋብሪካ ተመረቀ

በዓመት 1 ነጥብ 4 ሚሊየን ቶን የማምረት አቅም ያለው ሐበሻ ሲሚንቶ ፋብሪካ ዛሬ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በተገኙበት ተመርቋል።

ፋብሪካውን መርቀው የከፈቱት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፥ ከ16 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን እውቀታቸውን እና ገንዘባቸውን አንድ ላይ በማምጣት ያቋቋሙት ይህ ፋብሪካ የመደራጀት ጥቅምን ያሳየ ነው ብለዋል።

ፋብሪካው በሀገሪቱ ዜጎች አቅም ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ማሳያ ነው ሲሉም አስረድተዋል።

የዛሬ 10 ዓመት የሀገሪቱ ሲሚንቶ የማምረት አቅም በዓመት 1 ነጥብ 8 ሚሊየን ቶን ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በዛሬው እለት ሀበሻ ሲሚንቶ ፋብሪካ ወደ ስራ መግባቱን ተከትሎ የሀገሪቱ ሲሚንቶ የማምረት አቅም በዓመት ወደ 16 ነጥብ 4 ሚሊየን ቶን ከፍ እንዳለም አስታውቀዋል።

ይህም አሁን ላይ በሀገሪቱ በስፋት እየተከናወነ የሚገኘውን የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ፥ ይበልጥ የሚያነቃቃ እና ተጨባጭ ለውጥ እንዲመጣ የሚያስችል ነው ብለዋል ።

የፋብሪካው ወደ ስራ መግባትም በሁለተኛው የእድገት እና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን መጨረሻ፥ አጠቃላይ የሲሚንቶ ምርትን ወደ 27 ሚሊየን ቶን ለማድረስ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት ትልቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ የሲሚንቶ ምርቶችን ከውጭ ታስገባ ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ አሁን ላይ ግን በርካታ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በሀገሪቱ በመገንባታቸው የሀገር ውስጥ ፍላጎቷን በማሳካት ወደ ውጭ መላክ መጀመሯንም አስታውቀዋል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ አብተው በበኩላቸው፥ የፋብሪካው ወደ ስራ መግባት በከፍተኛ እድገት ውስጥ ላለው የግንባታ ዘርፍ ተጨማሪ መነቃቃትን የሚፈጥር ነው ብለዋል።

በዛሬው እለት የተመረቀው ሀበሻ ሲሚንቶ ፋብሪካ ከአዲስ አበባ በ35 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው የሆለታ ከተማ አካባቢ ነው የተቋቋመው።

ከ155 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ በሆነ ወጭ የተገነባው ፋብሪካው፥ በ16 ሺህ 500 ኢትዮጵያውያን እና በሁለት የደቡብ አፍሪካ ኩባንያዎች አማካኝነት የተመሰረተ መሆኑም ተነግሯል።

ሁለቱ የደቡብ አፍሪካ ኩባንያዎችም ፕሪቶሪያ ፖርትላንድ ሲሚንት እና ኢንዱስትሪ ዴቭሎፕመንት ኮርፖሬሽን የተባሉ ናቸው።

ፖርት ላንድ ፖዞላና እና ኦርዲናሪ ፖርት ላንድ ሲሚንቶዎችን የሚያመርተው ይህ ፋብሪካ ለሀገሪቱ የግንባታ ኢንዱስትሪ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሏል-(ኤፍ.ቢ.ሲ)።