ኢትዮ-ቴሌኮም የአጭር መልዕክት አገልግሎት የሚሠጡ 40 ኩባንያዎች ማገዱን አስታወቀ

ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በአጭር የጽሑፍ መልዕክት አገልግሎት ከሚሰጡ ከ180 በላይ ኩባንያዎች ውስጥ 40ዎቹ መታገዳቸውን ኩባንያው ይፋ አደርጓል፡፡

ኩባንያዎቹ ያለአግባብ ከደንበኞች ገንዘብ የቆረጡ ኩባንያዎችን በፍርድ ቤት ጭምር የወሰዱትን ገንዘብ እንደሚያስመልስ ኢትዮ ቴሌኮም አስታውቋል፡፡

ኩባንያዎቹ ከቴሌኮም ደንበኞች ከ23 ሚሊዮን ብር በላይ ያለአግባብ መቆረጣቸውም ነው ኢትዮ-ቴሌኮም ገልጿል ።

በኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሪት ፍሬህይወት ታምሩ የደንበኞች አቤቱታ ኩባንያው እየደረሰው ስለመሆኑ ገልፀው በአጭር የሞባይል መልዕክት የሚሰጠው አገልግሎት ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ውል በገቡ ኩባንያዎች አማካይነት የሚሠራበት ዘርፍ ነው፡፡

አገልግሎቶቹ በኢንፎሜሽን የበለፀገ ማህበረሰብ ከመገንባት አንፃር ሚናቸው እንደሚጎላ ጠቁመው፣ የአገልግሎት አሰጣጣቸው ግን መፈተሽ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

ኩባንያዎቹ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በገቡት የውል ግዴታ መሠረት መሥራት ቢጠበቅባቸውም፣ አንዳንዶቹ ከውል ውጭ በሆነ መንገድ ስለሚሠሩ ችግሮች እንደሚታዩ፣ ከእነዚህ ችግሮች መካከልም ደንበኞች ያለፍላጎታቸው መልዕክት እንደሚደርሳቸው ኃላፊዋ ተናግረዋል ።

 ከደንበኞች ያለአግባብ ገንዘብ የቆረጡ ኩባንያዎች ፍርድ ቤት በመውሰድ ጭምር የወሰዱትን ገንዘብ ለማስመለስ እንደሚሠራ ኢትዮ ቴሌኮም አስታውቋል።