የነዳጅ እጥረት የተከሰተው ነዳጅን በህገ ወጥ ተግባር የማሸሽ ሂዴት በመከናወኑ እንደሆነ ተጠቆመ

በኢትዮጵያ ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ የተከሰተው የነዳጅ አቅርቦት ችግር ሰው ሰራሽ የሆነ ነዳጅን የማሸሽ ህገ ወጥ ተግባር በመከናወኑ እንደሆነ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጠቁሟል።

የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነትና የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሃላፊ አቶ ወንድሙ ፍላቴ እንደገለጹት በምርት አቅርቦት ዙሪያ በሚፈጸም ደባ ያለምንም ኢኮኖሚያዊ ምክንያት እጥረት ተፈጥሯል።

ነዳጅ የሚያከፋፍሉ ኩባንያዎች ከተፈቀደላቸው የነዳጅ ማራገፊያ ስፍራ ውጪ በማራገፍ እጥረቱ እንዲፈጠር ማድረጋቸውን ጠቁመዋል።

ነዳጅ በጥቁር ገበያ በበርሜልና በጄሪካን ጭምር እንዲሸጥ በማድረግ በኮንትሮባንድ የመነገድ ተግባርና ነዳጅ መልሶ ከአገር እንዲወጣ የማድረግ ህገ ወጥ ተግባር መስተዋሉንም አቶ ወንድሙ ተናግረዋል።

ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ወይም ደግሞ ግብይትን ለማዛባት በተደረገ እንቅስቃሴ ባለፉት ሳምንታት የነዳጅ እጥረት እንዲፈጠር መደረጉንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ ታደሰ ኃይለማሪያም በበኩላቸው የነዳጅ አቅርቦቱ በዕቅዱ መሰረት የተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

ሰሞኑን የተከሰተው የነዳጅ እጥረት ሰው ሰራሽ መሆኑን ተናግረው ቤንዚንን ብቻ ለአብነት በማንሳት በአማካኝ የሚያስፈልገው 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሊትር ነዳጅ እየቀረበ መሆኑን ገልጸዋል።

ባለፉት ሶስት ወራት የሚፈለገው ያህል የነዳጅ ስርጭት እየተካሄደ እንደሆነም አመልክተዋል።

ከሱዳንና ከጂቡቲ ወደቦችም የሚያስፈልገውን ያህል ነዳጅ እንዲገባ እየተደረገ ስለመሆኑ በመግለጽ የአቅርቦት ክፍተት ያለመኖሩን ተናግረዋል።

የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነትና የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊው አቶ ወንድሙ ነዳጅ የሚያጓጉዙ ኩባንያዎች ነዳጅ ከማደያ ውጪ መሸጥ እንደሌለባቸው አስገንዝበዋል።

ድርጊቱን ሲፈጽም የተገኘ አካል በህግ የሚጠየቅ መሆኑንም አስገንዝበዋል።

በህግ ከመጠየቅ ባለፈ ነዳጅ የመገልበጥ ስራ ጥንቃቄ የሚፈልግና ለአደጋ የሚያጋልጥ በመሆኑ ከድርጊቱ መቆጠብ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህ ከፍተኛ ወጪ እየተደረገበት ወደ አገር ውስጥ የሚገባው ምርት ከፍተኛ ትኩረት የሚሻ ሲሆን ችግሩን ለመቅረፍም በእቅድ እየተሰራበት እንደሆነ ነው አቶ ወንድሙ የገለጹት።

በታሪፍ ጭማሪ ምክንያት የተነሱትን ጥያቄዎችን ለነዳጅ ጫኝ ተሽከርካሪ ባለንበረቶች በጥናት የሚመለስ እንደሆነም ተገልጿል።

ነዳጅ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ከተሞች በህገ ወጥ መንገድ እየተሸጠ እንደሚገኝ የሚገልጹት አቶ ወንድሙ ህብረተሰቡ ህገ ወጥ ስራውን እንዲጠቁም ጠይቀዋል።

ኢትዮጵያ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ወጪ በማድረግ ወደ አገር ከምታስገባቸው ምርቶች ውስጥ አንዱ ነዳጅ ሲሆን በአመት 3 ቢሊዮን የአሜረካ ዶላር ትከፍላለች። (ኢዜአ)