አዲስ አበባ በአየር ትራንስፖርት የአፍሪካ መግቢያነትን ከዱባይ መረከቧ ተገለጸ

ኢትዮጵያ ወደ ተለያዩ አፍሪካ ሀገራት  የሚጓዙ የአየር ትራንስፖርት ተጠቃሚዎችን በማስተናገድ ቀዳሚነቱን ከዱባይ መረከቧ ተገልጿል።

ፎርዋርድኬይ የተሰኘ የጉዞ አማካሪ ድርጅት ይፋ እንዳደረገው የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የአፍሪካ መግቢያ የመሆን ሚናን ከዱባይ ተረክቧል።

ፎርዋርድኬይ ይህን ውጤት ይፋ ያደረገው በቀን ውስጥ የተጓጓዙ 17 ሚሊየን የአየር ትራንስፖርት ተጠቃሚችን መረጃ ከገመገመ በኋላ መሆኑ ተጠቁሟል።

በዚህም  በአዲስ አበባ በኩል  ከሰሃራ በታች ወደሚገኙ ሀገራት የሚጓዙ ሰዎች ቁጥር ከፈረንጆቹ 2013 ወደ 2017 የ85 በመቶ እድገት  አሳይቷል ተብሏል።

በተመሳሳይ እነዚህን ተጓዦች በማስተናገድ ቀዳሚ የነበረችው ዱባይ በተመሳሳይ ጊዜ የ31 በመቶ እድገት ማሳየቷን ድርጅቱ ይፋ አድርጓል።

በዚህ አመት ደግሞ አዲስ አበባ የ18 በመቶ እና ዱባይ የሶስት በመቶ እድገት ማስመዝገባቸውን መረጃው አመልክቷል።

እየተጠናቀቀ ካለው የፈረንጆቹ ህዳር ወር 2018 እስከ ፈረንጆቹ አዲስ ዓመት መግቢያ ድረስም የአውሮፕላን ማረፊያውን የሚጠቀሙ የኢትዮጵያ ዓየር መንገድ ተጓዦች ቁጥር በ40 በመቶ እንደሚያድግ ተጠቁማል።

የኢትዮጵያ ዓየር መንገድ የአፍሪካን ሰማይ መቆጣጠሩ እና ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ዓየር መንገዶች ጋር ድርሻ ወስዶ መስራቱ ለስኬቱ አንዱ ምክንያት መሆኑ ተጠቁማል።

በተጨማሪም በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እየተወሰደ ያለው የለውጥ እርምጃ በአለም አቀፉ ማህበረሰብ የተሰጠው በጎ ምላሽ እንደሆነም ተመልክቷል።

በተለይም ኢትዮጵያ አፍሪካውያን በመዳረሻ አውሮፕላን ቪዛ እንዲያገኙ መፍቀዷ እና በኦንላይን የቪዛ አገልግሎት መጀመሯ እንዲሁም በመንግስት ቁጥጥር ስር የነበሩ ግዙፍ ተቋማት ለግል ባለሀብቶች ክፍት እንደምታደርግ መግለጿ ለዕድገቱ ምክንያት ሆነዋል ነው የተባለው።

የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እየሰፋ መምጣት ከዚህ ቀደም ከሰሜን አሜሪካ ወደ አህጉሪቱ የሚመጡ አፍሪካውያን በለንደን፣ ፓሪስ እና ፍራንክፈርት የሚያደርጉትን እረፍት በመተው ቀጥታ ወደ አዲስ አበባ መብረር መጀመራቸውም ተመልክቷል።

በ345 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር እየተደረገለት ያለው ማስፋፊያም ሲጠናቀቅ አሁን ላይ 7 ሚሊየን የሆነው ዓመታዊ ተጓዦች የማስተናገድ አቅም ወደ 22 ሚሊየን ያድጋል ነው የተባለው።