መንግስት ባለፉት አራት ዓመታት በኮንትሮባንድ ምክንያት ከቀረጥ እና ታክስ 14 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር መሰብሰብ አልቻለም ተባለ

መንግስት ባለፉት አራት ዓመታት ወደ ሀገር ውስጥ ሲገቡ በተያዙ የኮንትሮባንድ ሸቀጦች ምክንያት ከቀረጥ እና ታክስ 14 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር መሰብሰብ ያለመቻሉን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ በሀዋሳ ከተማ ኮንትሮባንድ እና ህገወጥ ንግድን ለመከላከል ባዘጋጀው የምክክር መድረክ ላይ ነው ይህንን የገለጸው፡፡

በጥቅሉ ከ2007 እስከ 2010 ባሉት አራት ዓመታት ውስጥ ወደ ሀገር ውስጥ ሲገቡ የተያዙ ሸቀጦች የዋጋ ግምት 24 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር እንደሚያወጣ በስብሰባው ላይ ተጠቅሷል፡፡

እነዚህ ሸቀጦች የግብይት ደረሰኝ ስለማይቆረጥባቸው ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ መሰብሰብ እንደማይቻልም ተነስቷል።

በመድረኩ ላይ የታደሙት የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ኮንትሮባንድን የምንከላከለው ከሚያደርሰው የኢኮኖሚ ጉዳት በላይ የህብረተሰቡን ጤና አደጋ ላይ ስለሚጥል ነው ብለዋል።

በመሆኑም ህብረተሰቡ ኮንትሮባንድን እንዲጠየፈውና ለተጀመረው የህገወጥ ንግድ እና ኮንትሮባንድ መከላከል ስራ ትብብሩን እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

የገቢዎች ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዘመዴ ተፈራ ኮንትሮባንድ የውጭ ንግድን በማዳከሙ ምክንያት ከወጪ ንግድ መገኘት የነበረበት የውጭ ምንዛሬ ግኝት በየዓመቱ በአማካይ በ3 ነጥብ 82 በመቶ ቅናሽ እያሳየ መምጣቱን አንስተዋል።

በመድረኩ የፀጥታ ኃይሎች እና ህዝቡ ተባብረው ካልሰሩ ኮንትሮባንድ ከማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳቱ አልፎ የሀገር ደህንነት የስጋት ምንጭ እየሆነ መምጣቱ አይቀርም ተብሏል። (ኤፍ.ቢ.ሲ)