በህገ ወጥ መንገድ ሲጓጓዝ የነበረ ዘይት ተያዘ

የጉምርክ አሰራርን ሳያሟላ ወደ መቀሌ ሊገባ የነበረ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የምግብ ዘይት በቁጥጥር ሥር መዋሉ ተገለጸ።

በኢትዮጵያ ገቢዎች ሚኒስቴር የመቀሌ ቅርንጫፍ የኢንተሊጀንሲና ኮንትሮባንድ የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ገብረእግዚአብሄር ገብረህይወት እንደገለጹት ዘይቱ በአራት ተሳቢ ተሽከርካሪዎች ተጭኖ ከጅቡቲ ወደ መቀሌ ሊገባ ሲል በቁጥጥር ሥር ውሏል።

የምግብ ዘይቱ በቁጥጥር ስር የዋለው በህብረተሰቡ ጥቆማ አሸጎዳ በተባለው አካባቢ ነው፡፡

በተለያየ መጠን የታሸገው ዘይት 159 ሺህ 360 ሊትር እንደሆነ አስተባባሪው ተናግረዋል።

ዘይቱን ይዘው የመጡ ተሽከርካሪዎች የንብረቱን ዝርዝር መረጃ፣ የንብረቱ ባለቤትና የጉምሩክ ይለፍ ሰነዶችን ያለመያዛቸውን አመልክተዋል።

አሽከርካሪዎች  በቁጥጥር ስር ውለው ማጣራት ከተደረገ በኋላ በጉምሩክ መመሪያ መሰረት መለቀቃቸውን የተናገሩት አስተባባሪው፣ የንብረቶቹ ባለቤቶች ግን አልቀረቡም ብለዋል።

በተመሳሳይ ሁኔታ በምእራብ ሸዋ ዞን የቶኬ ኩታዬ ወረዳ ፖሊስ በህገ ወጥ መንገድ ሲጓጓዝ የነበረ ከ378 ሺህ ብር በላይ ግምት ያለው የምግብ ዘይት መያዙን ገለፀ፡፡

ዘይቱ የተያዘው በአይሱዙ የጭነት ተሽከርካሪ ከአዲስ አበባ ወደ ነቀምቴ በመጓጓዝ ላይ እንዳለ ነው፡፡

የወረዳው  ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ሳጂን አብዲሳ ጉሉማ እንዳሉት ፈቃድ ሳይኖረው በህገ ወጥ መንገድ ሲጓጓዝ የተገኘው 1ሺህ 800 ሊትር የምግብ ዘይት ሲሆን ከ378 ሺህ ብር በላይ ግምት አለው።

ዘይቱ ሊያዝ የቻለው በአሽከርካሪው ድርጊት ጥርጣሬ ያደረባቸው  የአካባቢ ነዋሪ ወጣቶች ለፖሊስ በሰጡት  ጥቆማ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡ (ምንጭ:- ኢዜአ)