ባለፉት 9 ወራት ከወርቅና ሌሎች ማዕድናት የተገኘው የውጭ ምንዛሬ ዝቅተኛ ነው ተባለ

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከወርቅና ሌሎች ማዕድናት የተገኘው የውጭ ምንዛሬ ግኝት ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ መሆኑን የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የፌደራልና የክልል ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት 3ኛው የማዕድን ስራዎች ምክር ቤት ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡

በዚህም የውጭ ምንዛሬ አቅምን የሚያሳድጉና ከውጭ የሚገቡ ማዕድናትን የሚተኩ የተለያዩ ማዕድናት እንዲመረቱ የሚያስችሉ የአሰራርና የህግ ማዕቀፎች መዘጋጀታቸውን ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡

በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት የውጭ ምንዛሬን አስመልክቶ በኩባንያዎች አማካኝነት 230 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ለማግኘት ታቅዶ መሰብሰብ የተቻለው ግን 5 ነጥብ 6 ሚሊየን ዶላር ብቻ ነው ተብሏል፡፡

የተገኘው ገቢ ከ2010 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ78 ነጥብ 5 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ገደማ ቅናሽ እንዳሳየ ተገልጿል፡፡

በባህላዊ መንገድ ከሚመረተው የወርቅ ምርት ደግሞ 537 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ 33 ነጥብ 6 ሚሊየን ዶላር መሰብሰቡንም ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡

ይህም ከ2010 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ38 ነጥብ 3 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ቅናሽ አሳይቷል ነው የተባለው፡፡

በአጠቃላይ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከወርቅና ሌሎች ማዕድናት የተገኘው የውጭ ምንዛሬ ግኝት ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ መሆኑ ተነግሯል፡፡