የመጀመሪያው የኢትዮጵያና ጣሊያን የቢዝነስ ጉባኤ በአዲስ አበባ ተከፈተ

የመጀመሪያው የኢትዮጵያና ጣሊያን የቢዝነስ ጉባኤ ዛሬ በአዲስ አበባ ተከፈተ፡፡

ጉባኤው የተከፈተው የጣሊያን ምክትል የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ፕሮፌሰር ኢማኑኤላ ኤልሮኤ እና ታዋቂ የጣሊያን ቢዝነስ ተቋማትና የአርባ ኩባንያዎች ተወካዮች በተገኙበት ነው፡፡

ኢትዮጵያና ጣሊያን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከጀመሩ 130 ዓመት የሞላቸው ሲሆን፣ የቢዝነስ ጉባኤውም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ሰፊ ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ጉባኤው ሁለቱ ሀገራት በንግድና ኢንቨስትመንት ያላቸውን ግንኙነት ይበልጥ ለማስፋት እንደሚያስችልም ተጠቁሟል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ትኩረት የሰጣቸው የኢኮኖሚ ዘርፎች በጉባኤው ላይ ተለይተው ትኩረት ይደረግባቸዋልም ተብሏል፡፡

የጣሊያን ኩባንያዎች ኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ያላትን የኢኮኖሚ አቅም እንደሚያጠኑና ኢትዮጵያም ከጣሊያን ኩባንያዎች ጥራት ያለውን የኢንዱስትሪና የቴክኖሎጂ ልምድ ለመካፈል እንደምትችል ተገልጿል፡፡

ግብርና፣ መሰረተ ልማት፣ የግብርና ቴክኖሎጂና ፕሮሰሲንግ፣ ሎጅስቲክስ፣ ጨርቃጨርቅና ቆዳ ምርቶች በጉባኤው ውይይት የሚደረግባቸው ዘርፎች መሆናቸውን ለጉባኤው በተዘጋጀው ጋዜጣዊ መግለጫ ለመረዳት ተችሏል፡፡