በድሬዳዋ ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡ ተገለጸ

በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን በከተማ አስተዳደሩ የገቢዎች ባለሥልጣን አስታወቀ።

ነጋዴዎችና ባለሙያዎች ምጣኔ ሃብቱ ከሚያመነጨው ሃብት ጋር የሚመጣጠን ገቢ ለመሰብሰብ ህገ-ወጥን ንግድን መከላከል እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

በአስተዳደሩ በ2010 በጀት ዓመት ገቢው የተሰበሰበው ቀጥታና ቀጥታ ካልሆኑ ታክሶች እንዲሁም ከማዘጋጃ ቤታዊና ታክስ ካልሆኑ ገቢዎች ገቢ መሆኑን የባለሥልጣኑ የገቢ ጥናት ዕቅድ በጀት ዝግጅትና ክትትል ደጋፊ የሥራ ሂደት መሪ አቶ ዘውዱ አባይ ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡

ባለስልጣኑ የዕቅዱን 76 ነጥብ 3 በመቶ ማሳካቱን ያስረዱት ኃላፊው÷ ዕቅዱን ሙሉ በሙሉ ያልተሳካው በአስተዳደሩ በነበረው አለመረጋጋትና በውጭ ንግድ መቀዛቀዝ ምክንያቶች እንደሆነ አስረድተዋል።

ሆኖም ገቢው ከ2009 በጀት ተመሳሳይ ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ15 ነጥብ 4 በመቶ ብልጫ እንዳሳየ ተናግረዋል፡፡

ባለሥልጣኑ በ2012 በጀት ዓመት 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ማቀዱ ተገልጿል።