በአዲስ አበባ ደረጃቸውን ያልጠበቁ የቤት ክዳን ቆርቆሮዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

በአዲስ አበባ በመጋዘኖች በተደረገ ድንገተኛ አሰሳ ደረጃቸውን ያልጠበቁ የቤት የክዳን ቆርቆሮዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የከተማዋ ንግድ ቢሮ አስታውቋል።

ምርቶቹ የተገኙት የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮና የአዲስ አበባ ከተማ የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በመሆን በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ባደረጉት የገበያ አሰሳ ነው።

የደረጃዎች ኤጀንሲ ምልክት የሌላቸውና ከደረጃ በታች የሆኑ ምርቶች በህጋዊ ብቻ ሳይሆን የንግድ ፈቃድ በሌላቸው መጋዘኖችም ወደተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ተጭነው ሊወጡ ሲሉ ነው በቁጥጥር ስር የዋሉት።

በተመመሳሳይ ከዚህ በፊት የተያዙ የቤት ክዳን ቆርቆሮዎቹ ናሙና ተወስዶ በተስማሚነትና ምዘና ኤጀንሲ በተደረገ የደረጃ ፍተሻ ደረጃውን ያላሟሉ መሆኑ መረጋገጡን አመልክቷል።

ከምርቶቹ መካከልም ቡሻን ቢ.ደቢሊው.ጂ 35 ፣ ጂንዳል በህንድ የተሰራ፣ ቡልሃን ቢ.ደብሊው.ጂ 34 ስማርት፣ ጂንዳል ትሬድ ማርክ ቢ.ደበሊው ጂ 34 የተሰኙ ምርቶች ይገኙበታል።

ቆርቆሮዎቹ ከውጭ አገራት በህጋዊም ሆነ በህገ ወጥ መንገድ ኬላ አልፈው እንደሚገቡ ገልጸው፣ በተስማሚነት ምዘና ኤጀንሲ ቤተ ሙከራ ተፈትሸው ደረጃዎችን የማያሟሉ ናቸው ብለዋል።

በቁጥጥር ስር የዋሉ መጋዘኖች በፍርድ ሂደት ውሳኔ እስኪየያገኙ ድረስ እንደሚታሸጉ፣ በድርጊቱ ተሳታፊ የንግድ ድርጅቶች በህግ ተጠያቂ እንደሚሆኑ  መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡