የከተማ አስተዳደሩ ከባንኮች ጋር በመሆን የከተማዋን ወጣቶች ተጠቃሚ የሚያደርግ የተቀናጀ ማዕከል ሊገነባ ነው

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከባንኮች ጋር በመሆን የከተማዋን ወጣቶች ተጠቃሚ የሚያደርግ የተቀናጀ ማዕከል ሊገነባ ነው፡፡

የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ ከሁሉም ባንክ ስራ አስፈፃሚዎች ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡

የከተማዋን ወጣቶች ተጠቃሚ ለማድረግ ባንኮቹ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር ለመስራት ፍላጎት እንዳላቸው ምክትል ከንቲባው ተናግረዋል፡፡

በዚህም ባንኮቹ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመተባበር ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያ (ፓርኪንግ ) እና የንግድ ማዕከልን አንድ ላይ ያጣመረ የተቀናጀ ማዕከል ለመገንባት እና ለወጣቶች ተጨማሪ የስራ ዕድል ለመፍጠር ከስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡

ምክትል ከንቲባው በበኩላቸው፣ የገቢ ግብርን ጨምሮ በንግድ ባንክ ብቻ ይሰጥ የነበረው እና በከተማ አስተዳደሩ ስር የሚሰበሰብ ማንኛውም የክፍያ አሰራር አገልግሎቱ በሁሉም የፋይናንስ ተቋማት(ባንኮች) ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ዙሪያ ጥናት እየተደረገ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በመጨረሻም የባንክ ስራ አስፈፃሚዎቹ የከተማ አስተዳደሩ ለመንግስት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ዩኒፎርምን ጨምሮ ሌሎች የትምህርት ቁሳቁሶችን ለማቅረብ እያደረገ ያለውን ተግባር ለመደገፍ ቃል ገብተዋል፡፡ መረጃው የከንቲባ ጽህፈት ቤት ነው፡፡