በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከኢነርጂ ሽያጭ ከ7 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ተገኝቷል

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በ2011 በጀት ዓመት ከኢነርጂ ሽያጭ ለመሰብሰብ ካቀደው 9.366 ቢሊዮን ብር ውስጥ 7.184 ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ 76.71 በመቶ ያህሉን ማሳካቱን አስታወቀ፡፡

ከዚህ ውስጥ ለአገልግሎት ተቋሙ የሚደርሰው 40 ከመቶ ብቻ ሲሆን፤ ቀሪው 60 ከመቶ የሚሆነው ኃይል ላቀረበው ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ያስተላልፋል፡፡

በበጀት ዓመቱ የተቋሙን የፋይናንስ አቅም ለማሳደግ መደበኛ የኃይል ፍጆታ ገንዘብ ስብሰባ ከማሻሻል ባሻገር አዳዲስ የገቢ ማሳደጊያ ማሻሻያዎችም ተከናወኗል፡፡

በዚህም ለኤሌክትሪክ መስመር ግንባታና ማስቀጠያ ስራ ከደንበኞች 15.54 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ፤ 5.6 ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ 36.04 በመቶ አፈፃፀም አሳይቷል፡፡

እንዲሁም ተቋሙ ከዚህ ቀደም ካልተከፈለ ውዝፍ ሂሳብ 1.07 ቢሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት ያቀደ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ 942.4 ሚሊዮን ብር በመሰብሰብ 88 ከመቶ አፈፃፀም ማሳየቱን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡