የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከጃፓን ኩባንያ አመራሮች ጋር ተወያዩ

የኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በጃፓን ታዋቂ ከሆኑት ኢቶቹ ኩባንያ፣ ሱሚቶሞ ኩባንያ እና ሚትሱቢሺ ኩባንያ ፕሬዝዳንቶች ጋር ኩባንያዎቹ በኢትዮጵያ ኢንቬስት ማድረግ በሚችሉበት ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።

ከኢቶቹ ፕሬዝዳንት ጋር በተደረገ ውይይት የኩባንያው ፕሬዚዳንት ዬሺሂሳ ሱዙኪ ኩባንያቸው ከኢትዮጵያ ጋር የረጅም ጊዜ የንግድ ግንኙነት እንዳለው ጠቅሰው፤ ከኢትዮጵያ የሠሊጥና የቡና ምርቶች ወደ ጃፓን በማስመጣት እንዲሁም ከጃፓን ወደ ኢትዮጵያ አይሱዙ መኪኖችን በማስመጣት የንግድ ልውውጥ ስራ ላይ እንደቆየ ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንቱ ይህንን የቆየ የንግድ ግንኙነት ማጠናከር የሚያስችል ኢንቨስትመንት ላይ ለመሳተፍ ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀው፤ በተለይ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ለመመስረት የሚያስችላቸው የመግባብያ ስምምነት መፈራረማቸውን ገልፀዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በበኩላቸው በኢቶቹ ኩባንያ እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴ አድንቀው፤ ኩባንያው በተለይ ወደ ጃፓን የሚልካቸው የሰሊጥና የቡና ምርቶች ላይ እሴት በመጨመር መላክ ወደሚያስችለው የኢንቬስትመንት ተግባር ላይ እንዲያመራና እየተካሄደ ባለው የቲካድ ጉባኤም ቃል እንደተገባው ኢትዮጵያ ብሎም አፍሪካ ከጃፓን ኢንቨስትመንትና ቴክሎጂ ሽግግር ተጠቃሚ ልትሆን እንደሚገባ ገልፀዋል።

በተመሳሳይ ከሱሚቶሞና ከቶሺባ ኩባንያ ፕሬዝዳንቶች ጋር በተደረገ ውይይትም ድርጅቶቹ ወደ ኢትዮጵያ ገብተው በተለይ ታዳሽ ኃይል ማመንጨት እና በቴክኖሎጂ መስኮች ኢንቨስት እንዲደርጉ በውይይቱ የተሳተፉት የውሃ መስኖና፣ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለና ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶ/ር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ አብራርተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እንዲሁም በጃፓን የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር አቶ ካሳ ተክለብርሃን ለኩባንያዎቹ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ምንጭ:- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር