ኢትዮ-ጃፓን ቢዝነስና ኢንቬስትመንት ፎረም ተካሄደ

በዮኮሃማ ጃፓን እየተካሄደ ካለው 7ኛው የቲካድ ስብሰባ ጎን ለጎን ሁለተኛው የኢትዮ-ጃፓን የቢዝነስ ፎረምና ኤግዝቢሽን ተካሂዳል።

በዚሁ ፎረም 180 የጃፓን ባለሃብቶች እንዲሁም 43 የኢትዮጵያ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ተገኝተዋል።

በፎረሙ መክፈቻ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ በጃፓን የኢትዮጵያ አምባሳደር ካሳ ተክለብርሃን እንዲሁም የጃፓን የውጭ ንግድ ድርጅት (ጄትሮ) ፕሬዚዳንት ንግግር አድርገዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ባሰሙት ንግግር ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ሁኔታ የጃፓን ባለሃብቶችን ለማስተናገድ ዝግጁ መሆኗን አንስተው ፤ ባለሃብቶቹ ይህንን ምቹ ሁኔታ እንዲጠቀሙ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

አምባሳደር ካሳ ተክለብርሃን በበኩላቸው፣ ቶኪዮ የሚገኘው የኢፌዲሪ ኤምባሲ የጃፓን ባለሃብቶችን ወደ ኢትዮጵያ ለመላክ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ከተለያዩ ጃፓን ኩባንያዎችና ተቋማት ለሚደረግላቸው ድጋፍ በማመስገን ኤምባሲው ባለሃብቶቹ በኢትዮጵያ ያለውን አመቺ የንግድና ኢንቨስትመንት ዕድሎች እንዲጠቀሙ ሙሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደርም ለተሳታፊዎች የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት አመቺነት አስመልክቶ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

የጃፓን የውጭ ንግድ ድርጅት (ጄትሮ) ፕሬዚዳንት በኢትዮጵያ የተሻሻለ የንግድና ኢንቨስትመንት ዕድሎች እንዳሉ እንደሚያውቁና ይህንንም በየጊዜው ለአባላቶቻቸው እንደሚያስተዋውቁ ገልፀል።

በመድረኩ የኢትዮጵያ ኢንቨሽትመንት ምክትል ኮሚሽነር እንዲሁም የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ገለጻና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በአፍሪካ ልማት ዙሪያ ምክክር የሚያደርገው የቶኪዮ አለም አቀፍ ኮንፈረንስ (Tokyo International Conference on Africa Development) TICAD እ.ኤ.አ ከ1993 ጀምሮ አፍሪካ ከድህነትና ኃላቀርነት ለመውጣት የምታደርገውን ጥረት ለመደገፍ በጃፓን ጠንሳሽነትና አመራር ለአፍሪካ ልማት የሚካሄድ ኮንፈረንስ ሲሆን በጥምር አዘጋጅነት የአለም ባንክ፣ የተ.መ.ድ ልማት ድርጅት እንዲሁም የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡

ምንጭ:- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር