በሀምሌ ወር ከወጪ ንግድ ከ252 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ

በሀምሌ ወር ከወጪ ንግድ ከ252 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን መጨመሩን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

የ2012 ዓ.ም የሀምሌ ወር የወጪ ንግድ ገቢ አፈጻጸም ከአምናው ተመሳሳይ ወር ጋር ሲነጻጸርም በ40 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ወይም በ19 ነጥብ 23 በመቶ ብልጫ እንዳለውም ነው የገለፀው፡፡

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የወሩን ዕቅድ ሙሉ በሙሉ ማግኘቱን ጨምሮ አስታወቋል፡፡

በተጠቀሰው ወር 252 ነጥብ 19 የአሜሪካ ዶላር ለማግኘት አቅዶ የተገኘው ገቢ 252 ነጥብ 23 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር መድረሱን ገልጿል፡፡

በወጪ ንግድ ከፍተኛ መሻሻል ያደረጉ የግብርና ምርቶችም እንደ የጥራጥሬ ሰብሎች ፣የተፈጥሮ ሙጫና ዕጣን፣ ቡና፣ ቅመማቅመም፣ አበባ፣ አትክልትናፍራፍሬ፣ የቁም እንሰሳት፣ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ የተዘጋጀ ቅመም ፣የተዘጋጁ የፍራፍሬ ውጤቶች፣ የቅባት እህል ውጤቶች ሲሆኑ ፤ ሌሎቹ ደግሞ ኤሌክትሪክ እና ሌሎች ምርቶች ተብለው የተጠቀሱ ናቸው ፡፡

በአንጻሩ በማዕድን ዘርፍ ከፍተኛ ቅናሽ ያሳየ በመሆኑ ልክ እንደግብርና እና የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ  ዘርፍ የሚመለከተው አካላት ሁሉ ትኩረት በመስጠት ፣ክትትል ማድረግና የዘርፉን የወጪ ንግድ ገቢ እንዲንሰራራ እና እንዲበረታታ በከፍተኛ ደረጃ መሰራት እንዳለበት የሚኒስቴሩ ሪፖርት ያሳያል፡፡