ከቫይረሱ ተጋላጮች አንድ ሶስተኛ የሚሆኑት ወጣቶች እንደሆኑ ተገለጸ

በኢትዮጵያ በዓመት በኤች አይ ቪ ኤድስ ቫይረስ ከሚያዙ ከ16 ሺህ በላይ ሰዎች መካከል አንድ ሶስተኛው ያህሉ ወጣቶች መሆናቸውን የፌዴራል የኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

በአዲስ አበባ እየተካሄደ ባለው 4ኛው አገር አቀፍ የወጣቶች ኮንፍረንስ የጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ ፈይሳ ጥናታዊ ጽሁፍ ባቀረቡበት ወቅት እንዳሉት በሀገሪቱ  በኤች አይ ቪ ኤድስ የመያዝ  ቁጥሩ 90 በመቶ እየቀነሰ ቢመጣም አሁንም በቫይረሱ ተጋላጭ ከሆኑት ዜጎች   አብዛኛው  የወጣቱ  የህብረተሰብ ክፍል እንደሆነ ጠቁመዋል ፡፡

ለዚህ ዋነኛ ምክንያት አጠቃላይ ስለ ኤች አይቪ ኤድ ያለው ትኩረት ዝቅተኛና የተዛባ እየሆነ በመምጣቱ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

አሉታዊ የአቻ ግፊት፣ በዕድሜ አቻ ካልሆኑ ሰዎች ጋር 60 በመቶ የሚሆኑ ወጣቶች የግብረ ስጋ ግንኙነት በመጀመሪያና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እየጀመሩ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ወጣቱ ወሲብ ቀሰቃሸ የሆኑ ማህበራዊ ድህረ ገጾችን መመልከቱ ፣ አልኮልና አደንዛዢ ዕፅ ተጠቃሚነት መብዛት ወጣቱን ለኤች አይ ቪ ኤድስ ተጋላጭ እንዲሆን እያደረጉት እንደሆነም በጥናታዊ ጽሑፉ ተብራርቷል፡፡

መንግስት ለኤች አይ ቪ ኤድስ ይሰጠው የነበረው ትኩረት ለምን ቀነሰ?፣ ወጣቱን ከዚህ ችግር ለማዳንስ ምን እየሰራ ነው? የሚሉ ጥያቄዎችም ከተሳታፊ ወጣቶች ተነስተዋል፡፡

መድረኩን ያሰተባበሩት የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ከበደ ወርቁ እንዳሉት መከላከልን መሠረት ባደረገው የጤና ፖሊሲ አማካኝነት ወጣቶችን ከኤችአይቪ ኤድስና ከተለያዩ የአባላዘር በሽታዎች ራሳቸውን ለመጠበቅ የሚያስችልና የባህሪ ለውጥ እንዲያመጡ የሚረዱ ዘርፈ ብዙ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡

በሁሉም የጤና ተቋማት የምክርና አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎች እንዲደራጁ ተደርጓል፡፡ በዚህም አዲስ በኤች አይ ቪ ኤድስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በ90 በመቶ የቀነሰ ሲሆን በኤች አይ ቪ ኤድስ ምክንያት የሚከሰት ሞት ደግሞ ከ50 በመቶ በላይ ቀንሷል፡፡

አሁንም ከሀገሪቱ ህዝብ 30 በመቶ በላይ የሆነውን አምራች ወጣት ኃይል ከበሽታው ለመታደግ የሚያስችሉ አዳዲስ አሰራሮችን በመዘርጋት ትኩረት እንደሚሰጥም ዶክተር ከበደ ተናገረዋል፡፡

አጠቃላይ የኤች አይቪ ኤድስ ሥርጭት በአለም አቀፍ፣ በአህጉሩ አቀፍና በኢትዮጵያ ምን እንደሚመስል እስካሁን የተሰሩ ስራዎችና ቀጣይ አቅጣጫዎች ቀርበዋል፡፡