ውዳሴ ዲያግኖስቲክ ማዕከል በየዓመቱ በነፃ የሚሰጠውን ህክምና ለሰባተኛ ጊዜ ለመስጠት ምዝገባ ለመጀመር መዘጋጀቱን ይፋ አደረገ፡፡
ማዕከሉ የነፃ ህክምና መስጠት የጀመረው ከዛሬ ሰባት ዓመት በፊት ጀምሮ መሆኑን የማዕከሉ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዳዊት ሀይሉ ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም የነፃ ህክምናውን የሚፈልጉ አካላት በጳጉሜ አምስት ቀናት ውስጥ መመዝገብ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ለምዝገባ የሚያስፈልገውም ከመንግስት የህክምና ተቋማት የማዘዣ ወረቀት መያዝ ብቻ መሆኑን ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡
በተቀመጠው የአምስት ቀን የምዝገባ ቀነ ገደብ የተመዘገቡ ሰዎች የኤም አር አይና የሲቲ ስካን ህክምናን በነፃ ያገኛሉ፡፡ አንድ ሰው በአማካይ እስከ ሁለት ሺ ብር የሚደርስ ህክምና በነፃ እንደሚገኝም ነው የተመለከተው፡፡
ማዕከሉ 24 ሠዓት አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን የአምቡላንስ አገልግሎትም ይሰጣል፡፡ እስከ አሁን ድረስ ለ15ሺ ሰዎች ነፃ ህክምና የሰጠ ሲሆን በተያዘው ዓመት ከ800 እስከ 1000 የሚደርሱ ሰዎች አገልግሎቱን ያገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ማዕከሉ ተቋማዊ ማህበራዊ አገልግሎት የመስጠት ኃላፊነቱን በቀጣይም ይበልጥ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተመልክቷል፡፡
በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የአጠቃላይ ጤና ዘርፍ ዳይሬክተር ተወካይ ዶክተር ይበልጣል መኮንን ውዳሴ ዲያግኖስቲክ ማዕከል መንግስት የጀመረውን የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን የማስፋት ስትራቴጂ በከፍተኛ ደረጃ እያገዘ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ማዕከሉ አቅም ለሌላቸው ዜጎች በየዓመቱ የነፃ ህክምና መስጠቱ በጣም የሚበረታታና የሚደነቅ ተግባር እንደሆነም ዶክተር ይበልጣል አስገንዝበዋል፡፡ ሌሎች በተመሳሳይ ዘርፍ የተሰማሩ አካላትም ይህን መልካም አርዓያ ሊከተሉ እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት፡፡
ማዕከሉ ‹‹ጳጉሜን ለጤና›› በሚል ባዘጋጀው የውይይትና የምክክር መድረክ ላይ የተቋማዊ ማህበራዊ አገልግሎት ምንነትና ታሪካዊ ዳራ፣ የኤም አር አይና የሲቲ ስካን መሳሪያዎች አዎንታዊና አሉታዊ ተፅዕኖዎች የተመለከቱ ገለፃዎችና ማብራሪያዎች ቀርበዋል፡፡
የነፃ ህክምናውን ለማግኘት መመዝገብ የሚፈልጉ አካላት በስልክ ቁጥር 0940 10 10 10 ላይ በመደወል ዝርዝር መረጃዎቹን ማግኘት እንደሚችሉ ማዕከሉ አሳስቧል፡፡