ከልክ ያለፈ ውፍረት አዕምሮን በፍጥነት ያስረጃል ተባለ

በመካከለኛ የእድሜ ክልል የሚገኙ ከልክ በላይ ወፍራም ሰዎች አዕምሮ በፍጥነት እንደሚገረጅፍ አንድ ጥናት አመለከተ።

በካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ የተደረገውና በኒዮሮባዮሎጂ ኦፍ ኤጂንግ የታተመው ጥናት፥ ከፍተኛ የስብ ይዘት አዕምሯችን ከመደበኛው በ10 አመት ፈጥኖ እንዲያረጅ ያደርጋል ብሏል።

473 ከ20 እስከ 87 አመት እድሜ ያላቸው ተሳታፊዎች በሁለት ቡድን (ቀጭን እና በጣም ወፍራም) በሚል ተለይተው ጥናቱ ተደርጓል።

በዚህም የሰውነት ክብደታቸው ከቁመጣቸው አንፃር (ቦዲ ማስ ኢንዴክስ) ወይንም በሰውነታቸው ውስጥ የሚገኝ የቅባት መጠን ከ25 በላይ የሆኑ ሰዎች ቦዲ ማስ ኢንዴክሳቸው ከ25 በታች ከሆኑት ሰዎች ጋር ሲነፃፀር በአዕምሯቸው ውስጥ የሚገኝ ነጭ ቁስ (ኋይት ማተር) መጠን አነስተኛ መሆኑ ተረጋግጧል።

የተለያዩ የአንጎላችን ክፍል እርስ በርስ የሚያገናኙት ነጭ ቁሶች ለማስታወስ እና በፍጥነት ለማሰብ ይረዳሉ።

እነዚህ ህዋሳት በተፈጥሮ ከእድሜ መግፋት ጋር ተያይዞ የመኮማተር ባህሪ አላቸው። 

ከልክ በላይ በመወፈር እና ቦርጭ ምክንያትም ህዋሳቱ ሊጨማደዱ ይችላሉ ነው ያሉት በካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ የጥናቱ መሪ ፕሮፌሰር ሊዛ ሮናን።

ተመራማሪዎቹ የጥናቱን ተሳታፊዎች አዕምሮ ምስል ስካን ያደረጉ ሲሆን፥ የወጣቶቹ ወፍራም ሰዎች የአዕምሮ አወቃቀር በመደበኛ ሁኔታ ከሚታየው የሽማግሌዎች የአዕምሮ አደረጃጀት ጋር ተመሳሳይ መሆኑን ተመልክተናል ብለዋል።

በርካታ የስብ ይዘት ያላቸው ህዋሳት “ሳይቶኪንስ” የተሰኙ ጎጂ ፕሮቲኖችን ሊያመርቱ ይችላሉ፤ ይህም አዕምሯችን ይጎዳል ነው ያሉት ፕሮፌሰር ሮናን።

በጥናቱ ከልክ በላይ የወፈሩ ሰዎች በሰውነታቸው ውስጥ ከፍተኛ የስብ መጠን ስለሚኖር ጤናማ ክብደት ካላቸው እኩዮቻቸው ጋር ሲነፃፀር የአዕምሯቸው እድሜ በ10 አመት የገረጀፈ ይሆናልም ብለዋል።

አጥኚዎቹ በአዕምሮ አስተሳሰብ ደረጃ ግን በወፍራም እና ቀጭን ሰዎች መካከል ምንም አይነት ልዩነት ማየት አለመቻላቸውን ተናግረዋል።

የጥናቱን ተሳታፊዎች የአስተሳሰብ ደረጃ በጊዜ ሂደት በተከታታይ ሰጠና ምናልባትም የተሳታፈዎቹ የአስተሳሰብ አቅም እየተዳከመ መሄዱን ያረጋግጣሉ ብለው እንደሚያምኑም ነው ያብራሩት።

በመሆኑም የሰውነትን ክብደት መቆጣጠር በአጠቃላይ የአዕምሯችን ጤና ለመጠበቅ ይበጃልና ያስቡበት ብለዋል ተመራማሪዎቹ።

በስዊድን ለ30 አመታት በ9 ሺህ መንትዮች ላይ በተደረገ ጥናት በመካከለኛ እድሜያቸው ከልክ ላለፈ ውፍረት የተጋለጡ መንትዮች መደበኛ ክብደት ካላቸው ጋር ሲናፃፀር ለአዕምሮ መቃወስ የመጋለጥ እድላቸው 80 በመቶ መሆኑ ተረጋግጧል።(ኤፍ.ቢ.ሲ)