ምግቦች ማቀዝቀዣ ውስጥ ለጅም ጊዜ ማስቀመጥ ለጤና ጠንቅ ይሆናሉ ተባለ

ምግቦች እንዳይበላሹና ብዙ ጊዜ ማቀዝቀዣ ውስጥ ማስቀመጥና ማቆየት የተለመደ ነው።

በዚህ መልኩ ምግብ ማቀዝቀዣ ውስጥ ማቆየቱ ምግቦችን እንደነበሩ በማቆየት ሳይበላሹ ለመጠቀም ያስችላል።

ይሁን እንጅ ምግቦችን ከተገቢው በላይ ማቆየትም ጉዳት እንዳለው በእንግሊዝ ከምቹ እና ጤነኛ የቤት አያያዝ ጋር በተያያዘ የሚሰራ ተቋም ይፋ አድርጓል።

እንደ ተቋሙ ገለጻ ምቹ እና ጽዱ መኖሪያ ቤትን ሲያስቡ የምግብ አያያዝ እና አጠቃቀም ላይ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም በማቀዝቀዣ ውስጥ ምግቦችን ለበዛ ቀናት ማስቀመጥ ጉዳት በማስከተል የጤና ጠንቅ ይሆናልና ያስቡበት ይላል።

እንደ ተቋሙ ገለጻ አብዛኛዎቹ ሰዎች ምግብን በማቀዝቀዣ ውስጥ ለበርካታ ጊዜ በማቆየት መቸ እና እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው አያውቁም፤ ይህ ደግሞ ብክነትንም ያስከትላል ብሏል።

ምናልባት የታሸጉ ምግቦች ከሆኑ ቶሎ መጠቀም ቢለመድም እንደ እንቁላል፣ ስጋና መሰል ምግቦችን ግን አብዝቶ በማቆየት ችግር ሲፈጠር እንደሚስተዋልም ነው ተቋሙ የሚያነሳው።

ተቋሙ ምግቦች በማቀዝቀዣ ውስጥ የሚቆዩበት ጊዜን በዚህ መልኩ አስቀምጦታል፤

አሳ 1 ቀን፣ ፍራፍሬዎች እንደ አስፈላጊነቱ እስከ 2 ቀን ድረስ

በአግድሞች የተቆረጡ ስጋዎች 2 ቀናት፣ ያልጠነከረ አይብ ከ2 እስከ 3 ቀናት፤

የበግ ቅልጥም እና የዶሮ ብልት ከ2 እስከ 3 ቀናት፤

ሰላጣ ከ2 እስከ 3 ቀናት፣ ቋሊማ 3 ቀናት፤

እንደ ቆስጣና ጎመን ያሉ አረንጓዴ አትክልቶች ከ3 እስከ 4 ቀናት፤

አፕል፣ ወይንና ማንጎን የመሳሰሉ ጠንካራ ፍራፍሬዎች ደግሞ ከ3 እስከ 7 ቀናት፤

ወተት ከ3 እስከ 4 ቀናት፣ ተጠብሶ የደረቀ የአሳማ ስጋ አንድ ሳምንት፤

ጠንካራ አይብ አንድ ሳምንት፣ እንቁላል አንድ ሳምንት፤

ሳልመን (ከአሳ ስጋ የሚዘጋጅ) እንደ አስፈላጊነቱ ከ1 እስከ 2 ሳምንት ይቆያል።

ከዚህ ባለፈ ግን ተቋሙ አሳን ጨምሮ የስጋ ተዋጽኦዎችን በታችኛው የማቀዝቀዣ ክፍል ላይ ማስቀመጥን ይመክራል፤ ከስጋው የሚወጣው ፈሳሽ ሌሎች ምግቦች ላይ እንዳይንጠባጠብ ስለሚረዳ።

ከእነርሱ ከፍ ብሎ ደግሞ ፈሳሽ ጭማቂና እንደ ቲማቲም ያሉና ሌሎች ደረቅ ያሉ አትክልቶችን ከፍ ብሎ ደግሞ ውሃ፣ እንቁላልና የታሸጉ ምግቦችን ማስቀመጥ።

አትክልቶችን፣ የታሸጉ ፈሳሽ ጭማቂና ማብሰያ ቅመሞችን፥ ከወተት፣ ከጥሬም ሆነ ከበሰለ ስጋ፣ ሳላድና አትክልቶች ጋር ማስቀመጥም መልካም መሆኑን ይመክራል-(ኤፍ ቢ ሲ)፡፡