ለጤና ጎጂ በመሆኑ እንዳይመረት ክልከላ የተደረገበት ''ኤክስል ኦሬንጅ'' ጭማቂ ለገበያ እየቀረበ በመሆኑ ህብረተሰቡ ጥንቃቄና ጥቆማ እንዲያደርግ በኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን የደቡብ ምዕራብ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡
የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ አድናን ሻሚል ለእንደገለጹት፤ በፓሲፊክ ኢንዱስትሪዎች ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የሚመረት ኤክስል ኦሬንጅ ጭማቂ ላይ በዋናው መስሪያ ቤት በኩል ከሶስት ወር በፊት በተደረገው የቤተ ሙከራ ፍተሻ ለጤና ጎጂና አደገኛ ሆኖ በመገኘቱ እንዳይመረት ታግዷል፡፡
ምርቱ ምንም አይነት የብቃት ማረጋገጫ የሌለውና ለጤና ጠንቅ በመሆኑም ከገበያ መሰብሰቡን አስታውሰዋል፡፡
የቅርጫፍ ጽህፈት ቤቱ የኢንስፔክሽን ባለሙያ አቶ ዳንኤል አሸብር በበኩላቸው፥ '''ኤክስል ኦሬንጅ'' ጭማቂ የሃገሪቱን የምግብ ደህንነትና ጥራት መስፈርት የማያሟላ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
"ባለፉት ሶስት ወራት ውስጥ ከ1 ሺህ 500 ደርዘን በላይ ''ኤክስል ኦሬንጅ '' ጭማቂ በአጋሮ፣ በጅማና በጊቤ የፍተሻ ማዕከላት በህገወጥ መንገድ ሲጓጓዝ ተገኝቶ እንዲወገድ ተደርጓል ነው ያሉት፡፡"
ጭማቂው በአሁኑ ሰዓት በገበያ ላይ እየዋለ የሚገኝ በመሆኑ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግም አሳስበዋል፡፡
ህብረተሰቡ ምርቱን በገበያ ላይ ሲያገኝም በነጻ የስልክ መስመር 8482 እንዲያሳውቅ ካልሆነም በአቅራቢያው ለሚገኙ የህግ አስከባሪ እና የጤና ተቆጣጣሪ አካላት እንዲጠቁም ጠይቀዋል-(ኢዜአ) ፡፡