በአለም አቀፍ ደረጃ ከሚደርሱ 10 የሞት አደጋዎች አንዱ በሲጋራ ማጨስ ምክንያት እንደሚከሰት አንድ አዲስ ጥናት ገለጸ።
በዓለማችን በሲጋራ ምክንያት ለህልፈት ከሚዳረጉት ውስጥ ግማሽ የሚሆኑት የአራት ሀገራት ማለትም የቻይና፣ ህንድ፣ አሜሪካ እና ሩስያ ዜጎች መሆናቸውም ተጠቁሟል።
ሀገራት ምንም እንኳን የትንባሆ መቆጣጠሪያ ፖሊሲዎችን ቢያወጡም ከህዝብ ብዛት ጨማሪው በእኩል ደረጃ የአጫሾች ቁጥር አያደገ መምጣቱን ነው በሜዲካል ጆርናል ላይ የወጣ ጥናት ያሳየው።
የሲጋራ አምራች ድርጅቶች በተለይም በማደግ ላይ ያሉ ሀገራትን ኢላማ አድርገው መንቀሳቀሳቸው የሟቾቹን ቁጥር እየጨመረ እንዲመጣ አድርጓል ተብሏል።
የጥናቱ ዋና ፀሃፊ ዶክተር ኢማኑኤል ጋኪዶአ እንደገለፁት፥ ባለፉት 50 አመታት ሲጋራ ማጨስ በጤና ላይ የሚያሳርፋቸው ጉዳቶች ተደጋግመው ቢገለጹም በአለማችን ከአራት ወንዶች አንዱ በየቀኑ ያጨሳል።
ማጨስ ያለ ጊዜ ለሚከሰት ሞት እና ለአካል ጉዳት በመዳረግ ረገድም በሁለተኛነት ተቀምጧል ነው ያሉት።
የግሎባል በርደን ኦፍ ዲዝዝ ሪፖርት እንደ አውሮፓውያኑ ከ1990 እስከ 2015 ድረስ የ195 ሀገራት ዜጎች የማጨስ ልማድ ምን ይመስላል የሚለውን ጥናት በማድረግ ነው የተሰራው።
በዚህም በ2015 በአለማችን 1 ቢሊየን የሚጠጉ ሰዎች በየቀኑ ሲጋራ እንደሚያጨሱ እና ከአራት ወንዶች አንዱ፤ ከ20 ሴቶች ደግሞ አንዷ እንደሚያጨሱ መረጋገጡን ሪፖርቱ ጠቁሟል።
የአጫሾች ቁጥር እንደ አውሮፓውያኑ 1990 ከነበረበት 870 ሚሊየን ነው በ2015 ወደ 1 ቢሊየን ያደገው።
ከሲጋራ ጋር በተያያዙ በሽታዎች የሚጠቁ ሰዎች ቁጥርም በ1990 ከነበረበት በ4 ነጥብ 7 በመቶ አድጎ በ2015 6 ነጥብ 4 ሚሊየን መድረሱን ሪፖርቱ አመላክቷል።
ጥናቱ አንዳንድ ሀገራት ዜጎቻቸው ሲጋራ ማጨስ እንዲያቆሙ በማድረግ ተሳክቶላቸዋል ይላል።
ከፍተኛ ታክስ መጣል፣ በማሸጊያዎች ላይ ማስጠንቀቂያዎችን መፃፍ እና የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብሮች መዘርጋት ሀገራቱ ላስመዘገቡት እድገት ምክንያትነት ከሆኑ ነጥቦች መካከል ተጠቅሰዋል።
ብራዚል በ25 አመታት ውስጥ በየቀኑ የሚያጨሱ ወንዶች ቁጥርን ከ29 በመቶ ወደ 12 በመቶ የቀነሰች ሲሆን፥ የሴት አጫሾችን ቁጥርም ከ19 በመቶ ወደ 8 በመቶ ዝቅ እንዲል ማድረግ ችላለች።
በባንግላዲሽ፣ ኢንዶኒዥያ እና ፊሊፒንስ ግን የአጫሾች ቁጥር በ25 አመታት ውስጥ ምንም ለውጥ አልታየበትም።
በሩስያ የሴት አጫሾች ቁጥር በ4 በመቶ ማደጉን ያሳየው ሪፖርቱ፥ ተመሳሳይ ችግር በአፍሪካ ሀገራትም እየታየ መምጣቱን የጥናቱ ፀሃፊ ዶክተር ኢማኑኤል ጋኪዶአ ተናግረዋል-(ኤፍ.ቢ.ሲ) ።