በወሊድ ጊዜ በደም መፍሰስ ምክንያት የሚከሰት የእናቶች ሞትን ለመከላከል የቅንጅት ሥራ ያስፈልጋል ተባለ

በወሊድ ጊዜ በደም መፍሰስ ምክንያት የሚከሰት የእናቶች ሞትን ለመከላከል
የቅንጅት ሥራ እንደሚያስፈልግ ተገለፀ፡፡

የሰው ልጅ እራሱን መተካት የተፈጥሮ ስጦታው ነው፡፡ ይሁን እንጂ ትውልድን የማስቀጠል ኃላፊነትን የምትወጣው እናት ሰው ለመተካት በምንም መመዘኛ ሂይወቷን ማጣት አይኖርባትም ፤ፍትሀዊም አይደለም፡፡

በወሊድ ምክንያት የሚከሰት ሞትን ኢፍትሀዊነት አጐልቶ የሚያሳየው ደግሞ ለመቆጣጠር በሚቻል ጥቃቅን ምክንያት የሚከሰት ሞት መሆኑ ነው፡፡

በወሊድ ምክንያት የሚከሰት ሞት በአብዛኛው የሚከሰተው ወይም 67 በመቶ የሚሆነው በወሊድ ጊዜ በሚከሰት ደም መፍሰስ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

በእርግዝና ጊዜ በሚከሰት የደም ግፊት፣ የደም ማነስ እና መሰል ምክንያቶች ናቸው፡፡ ሁሉንም በድምሩ ስንመለከት ከቅድመ ወሊድ ጀምሮ በጤና ተቋም የሚደረግ ክትትል ችግሩን በከፍተኛ ደረጃ ሊያቃልለው እንደሚችል መረዳት አያስቸግርም፡፡

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የእናቶች ጤና ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት ወ/ሮ ዘመዘም መሀመድ ይህንኑ ሃሳብ ያጠናክራሉ፡፡

 “በደም መፍሰስ ምክንያት የሚከሰት የእናቶች ሞትን በጋራ እንከላከል” በሚል መሪ ቃል በጥር ወር 2ዐ11 ዓ.ም የሚከበረውን የጤናማ እናትነት ወርን አስመልክቶ ለጋዜጠኞች ግንዛቤ ለማስጨበጥ በተዘጋጀ መድረክ ባለሙያዋ እንደተናገሩት በወሊድ ጊዜ እናቶችን ለሞት የሚዳርገው እናቶች ወደ ህክምና ተቋም እስኪደረሱ ድረስ መዘግየት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

እናቶች በቅድመ ወሊድ ጀምሮ በጤና ተቋምና በሰለጠነ ባለሙያ ክትትል እንዲያደርጉ ግንዛቤ ሊፈጠርላቸው እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

ባለፉት አመታትም የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የጤና ተቋማትን ተደራሽ ለማድረግና አገልግሎቱን በቅርበት ለመስጠት ባከናወናቸው ተግባራት በወሊድ ምክንያት የሚከሰት የእናቶቻቸው ሞትን 72 በመቶ መቀነስ መቻሉን የገለፁት ወ/ሮ ዘምዘም መሀመድ ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን ከ1ዐዐ ሺ እናቶች 412 የሚሆኑት በወሊድ ምክንያት እየሞቱ በመሆኑ ሁሉም አካላት በርብርብ ልንሰራበት ይገባል ብለዋል፡፡

በተለይ በደም መፍሰስ ምክንያት የሚከሰት የእናቶች ሞት ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዝ በመሆኑ እናቶች በወሊድ ግዜ ፈጥነው ወደ ህክምና ተቋም እንዲመጡ ማገዝ ይገባል ብለዋል፡፡

የፈሰሰውን ደም ለመተካትም የደም ልገሳ ሥራው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለማህበረሰቡ ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል ያሉት ባለሙያዋ፡ በዚህ ረገድ የሚዲያ ባለሙያዎች ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡

የጤናማ እናትነት ወርም ለህብረተሰቡ ግንዛቤ በሚፈጥሩ የንቅናቄ ሥራዎች እንደሚታሰብ አክለው ተናግረዋል፡፡