የኮሌራ ወረርሽኝን የሚተንብየው የኮምፒውተር ቴክኖሎጂ ለዓለም አዲስ ተስፋ እየሆነ መጥቷል

የኮሌራ ወረርሽኝን የሚተነብይ የኮምፒውተር ቴክኖሎጂ ለዓለም አዲስ ተስፋን የሰነቀ  ቴክኖሎጂ መሆኑ ተገለጸ ።

ባለፈው አመት በየመን የተከሰተውን የኮሌራ ወረርሽኝ  በእጅጉ መቀነሱ የተነገረለት ይህው የፈጠራ ስራ በሽታው ባለባቸው ሀገራት ሊሰራጭ እንደሆነ ተጠቆመዋል፡፡

በቅፅል ስሙ ‹‹የድህነት በሽታ›› ይሰኛል ንፅህናው ባልጠበቀና በተበከለ ውሃ አማካኝነት የሚተላለፈው የኮሌራ በሽታ፡፡

የአለም የጤና ድርጅት ይፋ እንዳደረገው ኢትዮጵያን ጨምሮ  በአለማችን በየዓመቱ መቶ ሺዎች በኮሌራ ለህልፈት ይዳጋሉ፡፡

ባለፈው ዓመት በየመን ብቻ 50 ሺህ ሰዎች በኮሌራ በሽታ ተጠቅተው ነበር። አሁን ላይ የኮሌራ በሽታ መተንበያ ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ ከዋለ በኋላ ግን ቁጥሩ ወደ 2500 ዝቅ ብሏል።

አዲሱ የመተንበያ ኮምፕዩተር የእርዳታ ሠጪ ሠራተኞችን ሥራ በእጅጉ ያቀለለ ሲሆን፤ የዝናብ ሂደትን በመከታተል ወረርሽኙ ከመከሰቱ ከሳምንታት በፊት መረጃው እንዲደርሳቸው ይረዳል።

የቅድመ መከላከል ሥራዎችን በአፋጣኝ ለማከናወን እጅግ ወሳኝ ፈጠራም ነው ተብሎለታል።

ባለፈው ዓመት በየመን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከውሃ ወለድ በሽታዎች ጋር በተያያዘ ለህመም ተዳርገው  ነበር። ከእነዚህ ውስጥ ከሁለት ሺ በላይ የሞቱ ሲሆን፤ አብዛኛዎቹ ደግሞ ህጻናት ናቸው።

ቁጥሩ በአለማችን ከፍተኛው ተብሎ የተመዘገበ ሲሆን፤ በየመን የተከሰተው የእርስ በእርስ ጦርነት የውሃ ፍሳሽና የንጽህና አገልግሎት መስጫዎችን ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጪ አድርጓቸዋል።

አዲሱ የፈጠራ ውጤት የዝናብና የአየር ንብረት ትንበያ ባለሙያዎች በመጀመሪያ እጅግ የተራቀቀ የተባለውን ኮምፕዩተር በመጠቀም እስከ 10 ኪሎሜትር ርቀት ውስጥ ባሉ ቦታዎች ምን ያክል ዝናብ የትኞች ላይ እንደሚዘንብ ይተነብያሉ።

እነዚህ ቁጥሮች የውሃ መውረጃዎች ውስጥ የሚገባው ውሃ ምን ያክል እንደሆነ ለማወቅና የወረርሽኙን መነሻ ለመለየት እጅግ ጠቃሚ ናቸው።

ከትንበያው የተገኙትን መረጃዎች በአካባቢው ካለው የህዝብ ቁጥር፤ የንጹህ ውሃ አቅርቦትና የአየር ጸባይ ጋር በማወዳደር የትኞች አካባቢዎች ላይ የኮሌራ ወረርሽኝ ሊነሳ እንደሚችል ማወቅ ይቻላል።

በመቀጠል የሚወሰደው እርምጃ የንጽህና አገልግሎት መስጫ መሳሪያዎችን፤ መድሃኒትና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን ቀድሞ ወደ ቦታው ሟጓጓዝ ነው። ለአካባቢው ነዋሪዎችም የቅድመ ጥንቃቄ ሥልጠና መስጠትና እንዲዘጋጁ ማድረግ ደግሞ ይቀጥላል።

ውጤቱም ገና ከአሁኑ እየታየ ነው፤ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ሰዎችን ከወረርሽኙ መከላከል የተቻለ ሲሆን፤ በየመን እየተሰራ ያለውን ስራም ወደ ሌሎች ቦታዎች ለማዳረስ እየታሰበ ነው።

በመላው ዓለም እስከ 30 ሺህ የሚደርሱ ሰዎች በየዓመቱ በኮሌራ ምክንያት ይሞታሉ። በዋነኛነት በወረርሺኙ የሚጠቁቱ ደግሞ አፍሪካውያንና ደቡብ እስያ አካባቢ የሚገኙ ሃገራት ናቸው ። (ምንጭ: ቢቢሲ)