ለተፈናቀሉ ዜጎች እየተሰጠ ያለውን የጤና አገልግሎት ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ተገለጸ

በተለያዩ ምክንያቶች ከቀየያቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች እየተሰጠ ያለውን የጤና አገልግሎት ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ተገለጸ፡፡

እስካሁን ተፈናቃይ ወገኖች በሚገኙባቸው ክልሎች ከ650 በላይ የጤና ባለሙያዎች በማሰማራት ድጋፍ መደረጉን የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ገልጿል፡፡

የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር በየነ ሞገስ እንደገለጹት በደቡብ ክልል ጌዲኦ ዞን ለሚገኙ ተፈናቃዮች ከሌሎች የጤና አገልግሎቶች በተጨማሪ የስነ አእምሮ ህክምና በመሰጠት ላይ ሲሆን በአጠቃላይ ከ660 በላይ ሰዎች ታክመዋል፡፡

አገልግሎቱን በሌሎች ተፈናቃዮች በሚገኙባቸው ክልሎች ለማስፋፋት እንዲቻል ለአማራና ለሶማሌ ክልል የጤና ባለሙያዎች ስልጠና ተሰጥቷል ነው ያሉት፡፡

በደቡብ ክልል 210 ሺህ ተፈናቃዮችን ማከም የሚያስችሉ የጤና መድሃኒቶችና ግብአቶች በክልሉ የመድሃኒት ማከማቻ በተጠባባቂነት እንዲቀመጥ ተደርጓልም ብለዋል፡፡

በአጠቃላይ በዚህ አመት ተፈናቃይ ወገኖች ለሚገኙባቸው ክልሎች ለሚሰጠው የጤና አገልግሎት 528 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ መደረጉም ተገልጿል፡፡

በአሁኑ ወቅት የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ የማቋቋም ስራ በሚሰራበት አከባቢዎች የጤና አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትና የጤና ባለሙያዎች እጥረት በመኖሩ ትኩረት ሊሰጠዉ እንደሚገባ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

ከዚህም ጋር በተያያዘ ተፈናቃይ ወገኖቻችንን ባሉበት አከባቢ በመሄድ በጤና ለማገልገል በጎ ፈቃደኞች በኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና እንስቲትዩት ማህበራዊ ድህረገፅ ላይ ከዛሬ ጀምሮ እንዲያመለክቱ ዶክተር በየነ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ 

(ምንጭ፡- የጤና ሚኒስቴር)