በአንድ ሳምንት 11 ሺህ ለሚጠጉ ተፈናቃዮች ህክምና ተሰጥቷል

ከሚያዝያ 9 እስከ ሚያዝያ 24 በነበረው የ1 ሳምንት ጊዜ ውስጥ በተለያዩ ክልሎች በሚገኙ 65 ወረዳዎች ለ10ሺህ 898 ተፈናቃይ ወገኖች ህክምና መሰጠቱን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ገልጿል፡፡

ኢንስቲትዩቱ በተለያዩ ምክንያቶች ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች እየተሰጠ ያለውን የጤና አገልግሎት አስመልክቶ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን ሳምንታዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

ከእናቶችና ህፃናት ጋር በተያያዘ፣ 16ሺህ 361 እናቶች የእርግዝና ክትትል ማድረጋቸውንና 734 ደግሞ የወሊድ አገልግሎት ማግኘታቸውን ኢስቲትዩቱ ጠቅሷል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ 648 እናቶች ከወሊድ በኋላ ክትትል ማድረጋቸውን እንዲሁም ለ11 ሺህ 926 ሴቶች የእርግዝና መቆጣጠሪያ አገልግሎት መሰጠቱ ተገልጿል፡፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ለተጎዱ ወገኖች የጤና ባለሙያዎች ቡድን ተልኮ የህክምና አገልግሎት መስጠቱም ተመልክቷል፡፡

በአሁኑ ወቅት 194 የጤና ባለሙያዎች በሱማሌ፣ አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች ተመድበው አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆናቸውም ተገልጿል፡፡

በጎ ፈቃደኞች ተመዝግበው አገልግሎት እንዲሰጡ በማህበራዊ ገጹ ጥሪ ማድረጉንና እስካሁን የተመዘገቡትን 176 ባለሙያዎች ለመመደብ ከክልሎች ጋር ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ኢስቲትዩቱ ገልጿል፡፡

የጤና ሙያ ማህበራት አባሎቻቸው በበጎ ፈቃደኝነት እንዲያገለግሉ እንዲያበረታቱም ኢስቲትዩቱ ጠይቋል፡፡

(ምንጭ፡- የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት)