በጤና ባለሙያዎች የቀረበው የደረጃ እድገት ጥያቄ ምላሽ አገኘ

በጤና ባለሙያዎች የቀረበው የደረጃ እድገት ጥያቄ ምላሽ ማግኘቱን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የጤና ባለሙያዎች የደረጃ እድገትን በተመለከተ ተደጋጋሚ ጥያቄዎችን ሲያነሱ መቆየታቸው ተገልጿል፡፡

በዚህም ከ2009 ዓ.ም ደመወዝ ጭማሪ ጋር ተያይዞ በፌደራል ሆስፒታሎች ወደ ጎን የነበረውን የደረጃ እድገት ከግንቦት 2011 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ላይ እንዲያድግ ተወስኗል፡፡

በተመሳሳይ በክልሎችም የደረጃ እድገቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ እንዲደረግ ለካቢኔ አቅርበው እንዲያስወስኑ ስምምነት ላይ መደረሱም ተገልጿል፡፡

በሌላ በኩል የጤና ባለሙያዎች በግላቸው የስፔሻላይዜሽን ስልጠና ለመወዳደር እና ለመማር የሚያስችላቸው እድል እንዲኖር ባነሱት ጥያቄ መሰረት የጤና ሚኒስቴር የስፔሻላይዜሽን ፈተና በግል ወስደው መሰልጠን ለሚፈልጉ ባለሙያዎች በየአመቱ መንግስት ከሚያስተምራቸው የስፔሻላይዜሽን ህክምና ትምህርቶች መካከል መስከረም ላይ በውይይት ከሚወሰነው ከአጠቃላይ ኮታ ላይ ለግል አመልካቾች በሚፈቀደው ኮታ መሰረት የስፔሻላይዜሸን ትምህርት እንዲከታተሉ ተፈቅዷል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ባለፈው ሚያዚያ 26፤ 2011 ዓ.ም ከሀገሪቱ ከተውጣጡ ከጤና ባለሙያዎች ጋር በመወያየት የተለያዩ ጥያቄዎችን ማንሳታቸው ይታወሳል፡፡

(ምንጭ፡-የጤና ሚኒስቴር)