ጤናማ ያልሆነ ውፍረት ከከተሞች ይልቅ በገጠር በፍጥነት እየጨመረ መጥቷል- ጥናት

ጤናማ ያልሆነ ውፍረት ከከተሞች ይልቅ በገጠር በፍጥነት እየጨመረ እንደመጣ አዲስ ጥናት አመለከተ፡፡
ከልክ ያለፈ ውፍረት ጤናማ ባልሆኑ የአመጋገብ እና የአኗኗር ዘይቤዎች ምክንያት በዋነኝነት በከተሞች የሚከሰት ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ መሆኑ ነበር እስካሁን የሚታወቀው።

በሥራ ሰዓት ለረጅም ጊዜ መቀመጥ፣ የኢንተርንት ጌም ሱሰኛ መሆን፣ በተቀነባበረ ምግብ ውስጥ የሚገኝ ስኳር፣ ጨው እና የተከማቸ ስብ፣ በውጥረት ላይ የተመሠረተ አመጋገብ፣ ያልተለመዱ የአመጋገብ ስርዓቶች ሁሉ የከተማ ህይወት ገፅታዎች ናቸው።

ይህ ደግሞ የከተማ ነዋሪዎች ከመጠን በላይ እንዲወፍሩ ማድረጉ ነበር በስፋት የሚነገረው።

አሁን ግን ከልክ ያለፈ ውፍረት ከከተሞች ይልቅ በገጠሮች በስፋት መታየት መጀመሩን ነው አዲስ ጥናት ያመለከተው።

በፈረንጆቹ 1985 እና በ2017 መካከል ባለው ጊዜ ከ190 አገሮች 112 ሚሊየን በከተማና በገጠር የሚኖሩ ጎልማሶችን ያካተተ ዓለም አቀፍ የሰውነት ምጣኔ (ቦዲ ማስ ኢንዴክስ) ጥናት ተካሂዶ እንደነበርና ውጤቱም በኔቸር መጽሔት ላይ እንደወጣ ተጠቁሟል።

አጥኝዎቹ ቦዲ ማስ ኢንዴክስን ከ1 ሺህ ተመራማሪዎች ኔትወርክ ጋር በማጣመር የየሰውን ቁመትና ክብደት ለክተዋል። በጥናቱ መሰረት በ3 አሥርተ ዓመታት ውስጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሴቶች በ2 ኪሎ ግራም፤ ወንዶች ደግሞ በ2.2 ኪሎ ግራም በአማካይ ጨምረው እንደተገኙ ነው የተገለፀው።

ይህ ማለት በአሁኑ ወቅት እያንዳንዱ ሰው ከ5 እስከ 6 ኪሎ ግራም ጨምሯል ማለት ነው። ይሁን እንጂ ይበልጥ ትኩረት የሚስበው በዓለም አቀፍ ደረጃ ከግማሽ ሚሊየን በላይ የሚሆነው ጤናማ ያልሆነ ውፍረት የተከሰተው በገጠር አካባቢ መሆኑ ነው።

(ምንጭ፡- ዘሄልዝ ሳይት)