በአማራ ክልል ከ4 ሺህ 700 በላይ መደበኛ ደም ለጋሾች እንዳሉ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ

በአማራ ክልል ከ4 ሺህ 700 በላይ መደበኛ ደም ለጋሾች እንዳሉ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ አስታውቋል፡፡

በአማራ ክልል 10 የደም ባንኮች ያሉ ሲሆን፣ በእነዚህ የደም ባንኮች ውስጥ ደግሞ 1ሺህ 160 ቋሚ እና ተንቀሳቃሽ የደም መለገሻ ቦታዎች ይገኛሉ ተብሏል፡፡

111 የመንግስት እና የግል የጤና ተቋማትም ከ10ሩ የደም ባንኮች ደም የሚያገኙበት ከባቢያዊ ትስስርም ተፈጥሮላቸዋል፡፡ ከሦስት ጊዜ በላይ ደም የለገሰ ሰው ‹‹መደበኛ ለጋሽ›› እንደሚባል በአማራ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ በፈውስ ህክምና የስራ ሂደት የደም ባንክ አገልግሎት ኬዝ ቲም አስተባባሪ አቶ አንዳርጌ አጥናፉ ተናግረዋል፡፡

በክልሉ ከ4 ሺህ 700 በላይ መደበኛ ለጋሾች እንደሚገኙም የገለጹት አቶ አንዳርጌ፣ በክልሉ ከሚሰበሰበው ደም ውስጥ 66 በመቶ የሚሆነው የሚገኘው ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ለጋሾች በክረምት ለእረፍት ወደየቤተሰቦቻቸው ስለሚሄዱ ከፍተኛ የደም እጥረት እንደሚከሰትም አስገንዝበዋል፡፡ በክረምት የሚስተዋለውን የደም እጥረት ለመቅረፍ የሚዲያ ፎረም ተቋቁሞ በተለያዩ ሁነቶች ላይ ደም ለመሰብሰብ ጥረት እየተደረገ ቢሆንም በተፈለገው መጠን ማግኘት አለመቻሉን አቶ አንዳርጌ ተናግረዋል፡፡

ደም የተለያዩ ሁነቶች በሚኖሩባቸው ቦታዎች ሁሉ በተንቀሳቃሽ መንገድ እና በቋሚ የመለገሻ ጣቢያዎች ይሰበሰባል፤ በተቻለ መጠን ግን ደም ለጋሾች በቋሚ የመለገሻ ጣቢያዎች እየተገኙ እንዲለግሱ ጠይቀዋል፡፡

በ2011 የበጀት ዓመት 18 ሺህ 400 ዩኒት ደም ለመሰብሰብ ታቅዶ 14 ሺህ 395 ዩኒት ደም በመሰብሰብ የዕቅዱን 76 በመቶ ማሳካት እንደተቻለ ገልጸዋል፡፡

ከ18 እስከ 64 ዓመት የዕድሜ ክልል ያሉ፣ ክብደታቸው ከ45 ኪሎ ግራም በላይ የሆኑ እና ከለገሱ ከሦስት ወር በላይ የሆናቸው ሰዎች ደም መለገስ ይችላሉ፡፡

ደም መለገስ በለጋሹ ጤና ላይ የሚፈጥረው ምንም አይነት ጉዳት የለውም፡፡ ሆኖም ግን ለደም እጥረቱ ምክንያት የማኅበረሰቡ የግንዛቤ እጥረት እና የተሳሳተ አመለካከት በመሆኑ የግንዛቤ ፈጠራ በሰፊው ለመስራት ማቀዳቸውን አቶ አንዳርጌ ተናግረዋል፡፡

‹‹ደም በመለገስ የሰውን ልጅ ህይዎት መታደግ ይቻላል›› ያሉት አቶ አንዳርጌ ደም በመለገስ እና ግንዛቤ በመፍጠር ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል፡፡(ምንጭ፡-አብመድ)