የህክምና ክፍተቶችን አስቀድሞ ለመከላከል እየተሰራ ነው  

የጤና ሚኒስቴር የህክምና ክፍተቶችን አስቀድሞ ለመከላከል እየሰራ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡

በሀገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የህሙማን ደህንነት ቀን ሲከበር ነው ይህ የተገለፀው፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ10 ሰዎች አራቱ የህክምና ደህንነት ባለመረጋገጡ ምክንያት ህይወታቸውን እንደሚያጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

በዓመት ከ1 ሚሊየን በላይ ሰዎችም ከህክምና ደህንነት እጦት ጋር በተያያዘ እንደሚሞቱም ነው ጥናት የሚያመለክተው ፡፡

በኢትዮጵያ የህሙማን ደህንነት ቀን መከበር ታዲያ መሰል የህክምና ክፍተቶች ከመከሰታቸው አስቀድሞ ለመከላከልና የህሙማን ደህንነት ይበልጥ እንዲረጋገጥ ለማገዝ መሆኑን አቶ ያዕቆብ ሰማን በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የህክምና አሰጣጥ ዳይሬክቶሬት ጀነራል ዳይሬክተር ዛሬ በዓሉ በተከበረበት ወቅት ገልፀዋል፡፡

የህሙማን ደህንነትን ለማረጋገጥ የሚሰራ የሥራ ክፍል እና የቴክኒክ ኮሚቴ በሚኒስቴሩ ስር የተቋቋመ ሲሆን ፤የሥራ ክፍሉ ከህሙማን ደህንነት ጋር የተያያዙ ስልጠናዎችን የማዘጋጀት፣ የህግ ማዕቀፍ እንዲኖረውና የህክምና ስህተቶች እንዳይፈጠሩ ቀድሞ የመከላከል ስራዎች ይሰራል ተብሏል፡፡