የመድኃኒት የጎንዮሽ ክስተቶችን ለመቆጣጠር የሚያስችል አሰራር ይፋ ሆነ

አዲሱ የኤሌክትሮኒክ ሪፖርት ሥርዓትና የሞባይል አፕሊኬሽን መተግበሪያ ከመድኃኒት ጋር በተያያዘ የሚመጡ የጎንዮሽ ክስተቶችን በተሻለ መልኩ ለመቆጣጠርና ለተቆጣጣሪው አካል ሪፖርት ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን አዲሱን የኤሌክትሮኒክ ሪፖርት ሥርዓትና የሞባይል አፕሊኬሽን መተግበሪያ ትናንት በኢንተር ኮንቲኔንታል ሆቴል ባስተዋወቀበት ወቅት የጤና ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን ቀደም ሲል በመላው ሀገሪቱ ከመድኃኒት የጎንዮሽ ክስተቶች ጋር በተያያዘ የሪፖርት ሥርዓቱ አስቸጋሪ እንደነበር አስታውሰዋል።

 አዲሱ የሪፖርት ሥርዓት በብዙ መልኩ ቀደም ሲል የነበረውን ችግር እንደሚቀርፈውና በተለይም መድኃኒቶች በሰዎች ላይ ችግር ሲፈጥሩ፣ የጥራት ጉድለት ሲኖርባቸውና መድኃኒት በስህተት በሚሰጥበት ጊዜ የሚፈጠሩ ችግሮችን በመመዝገብ ለሚመለከተው አካል በአፋጣኝ በመላክ መፍትሄ ለመፈለግ እንደሚያስችል ጠቁመዋል።

ለመድኃኒት ግዢ ብቻ ሀገሪቱ 2 ቢሊዮን ብር በየዓመቱ እንደምታወጣና ከ80 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎች መድኃኒቶችን እንደሚወስዱ የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ በመድኃኒቶች ጥራት ላይ በቂ ክትትል የማይደረግና የመድኃኒት ሥርዓቱ የማይስተካከል ከሆነ ሰዎች ለተለያዩ የመድኃኒቶች የጎንዮሽ ክስተቶች እንደሚጋለጡ ጠቁመዋል።አዲሱ የሪፖርት ሥርዓት ይህን ችግር በመፍታት በኩል በእጅጉ ጠቃሚ መሆኑን ገልፀዋል።

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ የኤሌክትሮኒክ ሪፖርት ሥርዓትና የሞባይል አፕሊኬሽን መተግበሪያ መምጣቱ ብቻ የሪፖርት ሥርዓቱን የተሳካ ሊያደርገው አይችልም።የተሳካ የሪፖርት ሥርዓት እንዲኖር በተለይ የጤና ባለሞያዎች ሥርዓቱን በትክክል እንዲጠቀሙ ማድረግና ለሥርዓቱ አስፈላጊ የሆኑ መሠረተ ልማቶችን ማዘጋጀት ይገባል።በዚህ ረገድ ባለሥልጣኑ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይጠበቅበታል።

በኢትዮጵያ በ2011 ዓ.ም 200 ሺ ከመድኃኒት ጋር የተያያዙ የጎንዮሽ ክስተቶች መፈጠራቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ። ከነዚህ ውስጥ 1 ሺ 400 የሚሆኑት ብቻ ሪፖርት እንደሚደረጉና ከዚህ ውስጥ በትክክል ሪፖርት የተደረጉት 500 ብቻ መሆናቸውን ከባለሥልጣኑ የወጡ መረጃዎች ያሳያሉ።

(ምንጭ፡- የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት)