ድንቅነሽ (ሉሲ) የሞተችው ከዛፍ ላይ ወድቃ መሆኑ በጥናት ተረጋገጠ

የመጀመሪያዋ የሰው ልጅ ቅሪት አካል ድንቅነሽ (ሉሲየሞተችው ከዛፍ ላይ ወድቃ መሆኑ በጥናት ተረጋገጠ።

ድንቅነሽ 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዓመት ያላት የመጀመሪያዋ የሰው ቅሪት አካል ስትሆን የተገኘችውም በአፋር ክልል ሃዳር በተባለው ቦታ 1966 . በአሜሪካውያኑ ዶክተር ዶናልድ ጆሃንሰንና ቶም ጌሪ መሆኑ ይታወቃል።

በኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣንና በአሜሪካው የአውስቲን ቴክሳስ ዩንቨርሲቲ ስምምነት መሰረት የሉሲ አጥንቶች የውስጥ ስብራቶች በሲቲ ስካን ቴክኖሎጂ ላለፉት ስምንት አመታት ሲጠኑ ቆይተዋል።

ይህ ጥናት ከአሁን በፊት ያልተመለሱ ጥያቄዎችን በመመለስ አዲስ እውቀት እንዲገኝ ማስቻሉም ተነግሯል።

በጥናቱ መሰረት የቀኝ እጇን ከትከሻዋ በሚያገናኘው አጥንቷ ላይ ያለው ስብራት ለየት ያለና የአሁን ዘመን ሰዎች ከታላላቅ ህንጻዎች ወይም ከገደል ሲወድቁ ከሚፈጠር ስብራት ጋር ተመሳሳይ ነው።

በዚህም የሉሲ አጥንቶች፣የራስ ቅል፣መንጋጋ፣የማህጸንና የጎን አጥንቶች የሁለቱም እግር ጉልበትና የቁርጭምጭሚት አጥንቶች ስብራት ሉሲ ከትልቅ ዛፍ ላይ ወድቃ ለመሞቷ ማረጋገጫ ሆኗል።

የዚህ ጥናት ፍሬ ነገርም ላለፉት 42 ዓመታት የሉሲን የሞት መንስኤና አኗኗር ሁኔታ ምላሽ ማግኘት ነበር።

በመሆኑም ሉሲ በጊዜው ወድቃ ረግራጋማ ቦታ በመቀበሯ ምክንያት 40 በመቶ አጥንቶቿ በጥሩ ሁኔታ እንዲገኙና አልፎ አልፎ ዛፍ ላይ ትኖር እንደነበር መረጋገጡን በጥናቱ የተሳተፉትና በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የፓልዮአንትሮፖሎጂ  ተመራማሪው  ዶክተር ሙሉጌታ ፍስሃ ተናግረዋል።

"ይህ ግኝት ስለ ሉሲ አዲስ የሳይንስ ዕውቀት እንዲኖረንና ሉሲ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የበለጠ ታውቃ እንድትጎበኝ ያደርጋል" ብለዋል።( ኢዜአ)