ተመራማሪዎች በህዋ ላይ “አስጋርዲያ” የተባለ አዲስ ሀገር እና ህዝብ ሊመሰርቱ መሆኑን አስታውቀዋል ።
አዲስ የሚመሰረተው ሀገር እና ህዝብ “አስጋርዲያ” የሚል ስያሜ የሰጡት ሲሆን፥ በዚህ ስፍራ በመሬት ላይ ያሉ ህጎች አይሰሩም ብለዋል።
የተመራማሪዎች፣ ኢንጅነሮች፣ የስራ ፈጠራ ባለቤቶች እና የህግ ባለሙያዎች ማህበር ከሰሞኑ ይፋ ባደረጉት መረጃ፥ በህዋ ላይ ራሱን የቻለ አዲስ ማህበረሰብ እንደሚመሰርቱ አስታውቀዋል።
አዲስ የሚመሰረተው ሀገር እና ህዝብ “አስጋርዲያ” ይባላል ያለው ማህበሩ፤ በምድር ላይ ካለው ከማንኛውም ሀገር ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌለው ገልጿል።
“አስጋርዲያ” በመጀመሪያ በመንኮራኩር ላይ የሚመሰረት ሲሆን፥ በኋላ ላይም እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጣር በ2017 በልግ ወራት ላይ ወደ ህዋ እንዲመጥቁ ይደረጋል ተብሏል።
ይህም “ስፑትኒክ” የሚባለው የመጀመሪያው መንኮራኩር ወደ ህዋ ከመጠቀ ከ60 ዓመት በኋላ ነው።
የ“አስጋርዲያ” ህዝብ እና ሀገር የራሱ የሆነ የህግ ማእቀፍ፣ ሰንደቅ ዓላማና ሌሎች አርማዎች ይኖሩታል የተባለ ሲሆን፥ ይህም በህዋ እድሜ ውስጥ አዲስ ምእራፍ መከፈቱን የሚያመልክት ይሆናል ተብሏል።
አስጋርዲያ እንደ እንድ ሀደር ራሱን የሚችል እና የሚያስተዳድር ሲሆን፥ ወደ ፊትም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አባል ሀገር ሆኖ ይመዘገባል የሚለውም ተብራርቷል።
አስጋርዲያን መመስረት ያስፈለገው ሰዎች በህዋ ላይ ሰላም እንዲያገኙ በማሰብ ነው፤ እንዲሁም በምድር ላይ ያለ ፀብ ወደ ህዋ በመሄድ ለማስቀረት ነው የሚለውንም ማህበሩ አብራርቷል።
በፕሮጄክቱ ዙሪያ የዓለም ህዝብ እንዲሳተፍ ድረ ገጽ የተዘጋጀ መሆኑም ተገልጿል።
ድረ ገጹ በመጀመሪያ ዙር 100 ሺህ ፍቃደኛ ሰዎች በምድር ላይ ካላቸው ዜግነት በተጨማሪ “የአስጋርዲያ” ዜጋ ሆነው እንዲመዘገቡ እድል የሚሰጥ ነው ተብሏል።
ዜጋ ለመሆን የሚመዘገቡ ሰዎች ቁጥር ከ100 ሺህ በሚበልጥበት ጊዜ አስጋርዲያን እውን ለማድረግ የተቋቋመው ማህበር ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደ አንድ ሀገር እንዲመሰረቱ ፈቃድ እንዲሰጣቸው የሚያመለክቱ ይሆናል ሲል ሚሮር ዶት ኮምን ጠቅሶ (ኤፍ.ቢ.ሲ) ሰግቧል ።