አሰር የአለማችን ቀጭን ላፕቶፕን ለገበያ አቀረበ

አሰር የአለማችን ቀጭን ላፕቶፕ ለገበያ አቅርቤያለሁ አለ።

ኩባንያው “ስዊፍት 7” የተባለውን ላፕቶፕ በ999 የአሜሪካ ዶላር ነው ለገበያ ያቀረበው።

አሰር ባለፈው ነሃሴ ወር ላይ ነበር በበርሊን በተካሄደው ዓለም አቀፍ የፊስካል ማህበር ኮንፈረንስ ላይ “የአለማችን ቀጭን ላፕቶፕ” ሰርቻለሁ ያለው።

የስዊፍት 7 ውፍረት ከ1 ሴንቲ ሜትር በታች 9 ነጥብ 98 ሚሊ ሜትር (0 ነጥብ 39 ኢንች) ሲሆን ክብደቱም 1 ነጥብ 1 ኪሎ ግራም ብቻ ነው ተብሏል።

የአሰር ስዊፍት 7 ባለፈው የፈረንጆቹ አመት ኤች ፒ ያስተዋወቀውን 10 ነጥብ 4 ሚሊ ሜትር ውፍረት ያለው “ስፔክትረ አልትራቡክ” በመተካት ነው የአለማችን ቀጭን ላፕቶፕ የሚለውን ስያሜ ያገኘው።

የአይ ፒ ኤስ ቴክኖሎጂ የተገጠመለትና 13 ነጥብ 3 ኢንች ስክሪን ስፋት ያለው ስዊፍት 7 የድምፅ እና ምስል ጥራቱም ከፍተኛ ነው ተብሏል።

ኢንቴል ኮር i5 ፕሮሰሰር፣ 256 ጌጋ ባይት ኤስ ኤስ ዲ እና 8 ጌጋ ባይት ራም ያለው የአሰር አዲስ ቀጭን ላፕቶፕ፥ አንድ ጊዜ ቻርጅ ተደርጎ እስከ 9 ስአት ማስጠቀም የሚያስችል ባትሪ ተገጥሞለታል።

በጥቁር እና በወርቃማ ቀለም የተሰሩ ስዊፍት 7 ላፕቶፕ ኮምፒውተሮችን ማዘዝ የሚፈልጉ ሰዎች በአማዞን በኩል በ999 የአሜሪካ ዶላር መግዛት ይችላሉ ብሏል አሰር።(ኤፍ.ቢ.ሲ)