በአሜሪካ ዳላስ ከተማ የሚገኙ ከ150 በላይ የሚሆኑ የአደጋ ጊዜ ሳይረኖች በአንድ ጠላፊ በመጠለፋቸው ምክንያት ሌሊት ላይ በመጮህ የዳላስ ከተማ ነዋሪዎችን መረበሹ ተገለጸ ።
የአደጋ ሳይረኖቹ አገልግሎት የሚሠጡት በዳላስ ከተማ እንደ ቶርኔዶ የመሳሰሉ አደጋዎች በሚከሰቱበት ወቅት ነው ።
ሆኖም አርብ ዕለት አንድ ጠላፊ የሳይረኑን መረጃ ማስተላላፊያ ሲስተም በመጥለፍ ለ90 ደቂቃ ሳይረኑ እንዲጮህ በማድረግ የከተማው ነዋሪዎች በሙሉ በለሊት ተደናግጠው እንዲነሱ አድርጓል ።
የዳላስ ከተማ የአደጋ ጊዜ አስተዳደር የቴክኒክ ኃላፊ እንደሚናገሩት ሳይረኑን እንዲጠፋ ስናደርግ ሲስተሙ መጠለፉን ተረድተናል ብለዋል ።
ጠላፊው ከዳላስ ከተማ ውስጥ የሚገኝ ነዋሪ እንደሚሆን የተገመተ ሲሆን ባለፈው ዓመትም በዳላስ ከተማ ብዙ የትራፊክ መብራቶችንና ምልክቶች ተጠልፈው ለቀልድ ፍጆታ እንዲውሉ መደርጉንና የአሁኑም ድርጊት በተመሳሳይ ሰው ሊፈጸም እንደሚችል ተጠቁሟል ። ( ምንጭ :ቢቢሲ )