የእጅ ስልክ ወድቆ እንዳይሰባበር የሚያደርግ የስልክ መያዣ ተሰራ

የእጅ ስልክዎ ወድቆ እንዳይሰባበር የሚያደርግ የሞባይል ስልክ ከቨር አልያም መያዣ ከወደ ጀርመን መሰራቱ ተገለጸ፡፡

በየጊዜዉ የሚሰሩ ዘመናዊ የእጅ ስማርት ስልኮች ካላቸዉ የካሜራ ጥራትና ሌሎች ዘመናዊ  ቴክኖሎጂዎች የገዢዎችን ቀልብ የሚስቡ ሲሆን ዋጋቸውም ከሌሎቹ ከፍ ባለ ዋጋ ለገበያ እንደምቀርቡ ይታወቃል፡፡

ይሁንና እንዲህ ከፍተኛ ወጪ ተደርጎባቸዉ የሚገዙ ስማርት ስልኮች ባልታሰበ ሁኔታ ድንገት ከእጅ አምልጠዉ ይሰበሩና ከጥቅም ዉጪ ሲሆኑ ማየት የተለመደ ነዉ፡፡

ለእንዲህ አይነት ችግር መፍትሄ ለመሻት  የስልክ አምራች ኩባያዎች የስልክ ሽፋን አልያም ከቨር ይሰራሉ፡፡ ሆኖም ግን አንዳንዴ ይህም ሆኖ ስልኮችን ከመሰበር ላይታደግ ይችላል፡፡

ለዚህ ሁሉ ሃሳብና ስጋት እፎይታ ሊሰጥ የሚችል መፍትሄ ታዲያ ከወደ ጀርመን ዩኒቨርሲቲ ተሰምቷል፡፡ ይህ ደግሞ የጀርመን ዩኒቨርሲቲ ተማሪ የሆነዉና ድንገት ከእጅም ሆነ ከተቀመጠበት ቦታ ቢወድቅ ከመሰበር ሊታደገዉ የሚችል የሞባይል ሽፋን ከቨር ሰርቷል ይለናል ከሲጂ ቲ ኤን ያገኘነዉ ዘገባ፡፡ 

በተለይም ደግሞ አዲስ ስልክ ገዝተዉ ምንም ሳይጠቀሙበት ስልኩ ሲሰበር ለማስጠገኛ የሚወጣዉ ወጪ አንዳንዴ ከስልኩ መግዣ ዋጋ ያልተናነሰ ሲሆን ይታያል፡፡ ተጠቃሚዎችም ከማስጠገን ይልቅ ሌላ አዲስ ስልክ በመግዛት ለተጨማሪ ወጪ ይዳረጋሉ፡፡

አሁን ግን ይህንን ሁሉ ኪሳራ የሚያስቀረዉና በጀርመን ዩኒቨርሲቲ ተማሪ የሆነዉ ፊሊፕ ፍሬንዜል የተሰራዉ የስልክ መሸፈኛ ከቨር ልክ ማንኛዉም ስልክ ላይ እንደሚደረገዉ የስልክ መሸፈኛ ከስልኩ ጋር በማያያዝ የሚሰራ ነዉ ተብሏል፡፡

የተሰራዉ አዲስ የስልክ መሸፈኛ ከቨር መጀመሪያ በተገጠሙለት  ሰንሰሮች አማካኝነት ስልኩ በምን አይነት ሁኔታ እንደተቀመጠ ማወቅ ያስችላል፡፡

ይህ የስልክ መሸፈኛ በተገጠመለት ሴንሰር አማካኝነት  ስልኩ በሚወድቅበት ቅፅበት በጠርዞቹ ላይ ያሉት ክንፍ መሳይ መሳሪያዎች ይዘረጉና ስልኩ ወደ ላይ እንዲነጥርና እንዳይሰነጠቅ ይረዱታል፡፡

ስልክ ወድቆ ከጥቅም ዉጪ እንዳይሆን የሚከላከል የስልክ ሽፋን ተጠቃሚዎች የእጅ ስልኮቻቸዉ ወድቆ ይሰበራል የሚለዉን ስጋት የሚያስቀር በመሆኑ ፈጠራዉ በተጠቃሚዎች ዘንድ ተወዳጅነት አግንቶታል፡፡ (ሲጂቲኤን)