ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሶፊያ የተሰኘችውን ሮቦት አነጋገሩ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሶፊያ የተሰኘችውን ሮቦት በጽህፈት ቤታቸው አነጋገሩ።

የእንግሊዘኛ ተናጋሪዋ ሮቦቷ ጥቂት የአማርኛ ቃላቶችን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ተለዋውጣለች።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት የሶፊያ ወደ ኢትዮጵያ መምጣትና አማርኛ ቋንቋን መሞከር አገሪቱን ከቴክኖሎጂው ዘመን ጋር የሚያቀራርብ ነው።

የሮቦቷ ስራ ከ60 በመቶ በላይ በኢትዮጵያዊያን እንደተሰራ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህም ኢትዮጵያዊያን ዕድሉን ካገኙ ብዙ መስራት እንደሚችሉ የሚያሳይ ነው ብለዋል።

ዕድሉን በመጠቀምም የሚመለከታቸው አካላት ተሰጥኦ ያላቸውን ወጣቶች በዘርፉ ለማሰማራት ማሰብ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

ሶፊያ የተሰኘችው የሰው የፊት ገጽታ ያላትና የሰው ስሜት በመረዳት ከሰው ጋር መነጋገር የምትችል ሮቦት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2013 መሰራቷ ይታወቃል።

ይህቺው ሮቦት በሰሞኑ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን የአይ ሲ ቲ ሳምንትን ምክንያት በማድረግ በኢትዮ-ቴሌኮም ስፖንሰር አድራጊነት በኢትዮጵያ የምትገኝ ሲሆን ዛሬ ማታ ወደ ህንድ እንደምታቀና ተገልጸዋል። (ኢዜአ)