ልጆች በስማርት ስልኮች ላይ የሚያሳልፉትን ቆይታ የሚቀንስ አዲስ ስክሪን አልባ ተንቀሳቃሽ ስልክ ተሰራ

በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን የልጆችን በስማርት ስልኮች ላይ የሚያሳልፉትን ቆይታ የሚቀንስ አዲስ ስክሪን አልባ ተንቀሳቃሽ ስልክ መሰራቱ ተሰምቷል፡፡

አሁን አሁን ተንቀሳቃሽ ስልኮች እየተበራከቱ የሰዉ ልጅም የእለት ተእለት እንቅስቃሴዉ ከእነዚህ ስማርት ስልኮች ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ሆኗል፡፡

ጥናቶች እንደሚያመላክቱት ጊዜአቸዉን አብዝተዉ ስማርት ስልኮቻቸዉ ጋር የሚያሳልፉ ሰዎች ለጤና ችግር ተጋላጭ መሆናቸዉን ይጠቁማሉ፡፡ በተለይም ደግሞ ህፃናት ላይ ችግር ከፍ እንደሚልም ጭምር፡፡

ታዲያ ይህንን ችግር መፍታት የሚያስችል መፍትሄ ሪፐብሊክ ዋየርለስ የተሰኘዉ ኩባንያ ሰርቷል ተብሏል፡፡ ኩባንያዉ የሰራዉ አነስተኛ ስማርት እና ስክሪን የሌለዉ ተንቀሳቃሽ ስልክ ለልጆች ታልሞ የተሰራ መሆኑን ገልፆ በተለይም ልጆች ከስማርት ስልኮች ላይ ለረጂም ሰዓታት አተኩረዉ የሚያጠፉትን ጊዜና የሚደርስባቸዉን  የጤና እክል ለመቆጣጠር እንዲያስችል ታስቦ እንደሆነም መረጃዉ ጠቅሷል፡፡

አነስተኛ እና ስክሪን የሌለዉ ይህ ስልክ በጎኑ ሁለት ስልኩን መክፈት የሚያስችሉ ቁልፎች ያሉት ሲሆን በተደጋጋሚ በመነካካት ብቻ ስልኩ የሚፈልጉትን ሙዚቃ አልያም ሌሎች ፕሮግራሞች ያስመርጣል፡፡

ምንም እንኳን የሚመርጡትን ፕሮግራም ስክሪን ላይ መመልከት የማይቻል ቢሆንም ድምፅ ወደ ስልኩ መላክም ያስችላል፡፡

ሌላዉ ትልቁ ነገር ደግሞ ልጆች የሚዝናኑበት ሙዚቃ እና ሌሎች የድምፅ መጫወቻዎች በተጨማሪ ሲም ካርድ የሚቀበልም ነዉ፡፡

ይህ ስክሪን የሌለዉ አነስተኛ ስልክ ስፒከር የሚመስል ሲሆን በስልኩ መሃል ላይ ያለ አነስተኛ ቁልፍ በመጫን ጥሪ መቀበልም ሆነ ጥሪ ማስተላለፍ ያስችላል፡፡

በስልኩ ጎን የሚገኙት ሁለት ቁልፎች ድምፅ ለመጨመር እንዲሁም ስልኩን ለማብራትና ብሎም  ለማጥፋት ያገለግላሉ፡፡

ሌላዉ ደግሞ በዚህ ስክሪን አልባ ስልክ የዋይ ፋይ አገልግሎት መጠቀም የሚያስችል እንደሆነም ተነግሯል፡፡

ሪለይ የሚል ስያሜ የተሰጠዉ ይህ ስክሪን አልባ ስልክ በተለይም ደግሞ ግላዊነትን የሚጠብቅ በመሆኑ ሌላኛዉ ተመራጭ ያደረገዋል፡፡ ለምሳሌ ስልኩ ሌሎች ኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች ያሉበትን ቦታ ይጠቁማል፡፡

ሌላዉ ይህ ስክሪን አልባ ተንቀሳቃሽ ስልክ የሚሰጠዉ ጥቅም ወላጆች ስማርት ስልኮቻቸዉ ላይ በሚጫነዉ መተግበሪያ ስክሪን አልባ ስልኩን የያዘዉ ልጅ የት እንዳለና ወዴት አቅጣጫ እንዳለ ማወቅ የሚያስችል እንደሆነም ተነግሯል፡፡

በአጠቃላይ ግን አሁን አሁን እያደገ የመጣዉንና በስማርት ስልኮች ላይ ልጆች ጥገኛ መሆን ችግር እንደሚፈታ ተስፋ ተጥሎበታል ሲል የዘገበዉ ዚዲ ኔት የተሰኘ ድረገፅ ነዉ፡፡