የፌስቡክ ተጠቃሚዎች የይለፍ ቃል ደህንነት አስተማማኝ አይደለም ተባለ

በሚሊዮን የሚቆጠሩ የፌስቡክ ተጠቃሚዎችን የይለፍ ቃል 20 ሺህ በሚሆኑ ፌስቡክ ውስጥ በሚሰሩ ሰዎች ይታወቁ እንደነበር ይፋ ተደርጓል።

የኢንተርኔት ደህንነት ተመራማሪው ብሬይን ክሬብስ ፌስቡክ የደንበኞችን መረጃ በመደበቅ ረገድ ችግር እንዳለበት አጋልጧል።

በጥናቱ መሰረት 600 ሚሊዮን የሚሆኑ የደንበኞች የይለፍ ቃል ምንም አይነት ጥበቃ ሳይደረግላቸው እንዲሁ ተጽፎ ለማንም ግልጽ በሆነ መልኩ እንደሚገኝ ተናግሯል።

እነዚህ የይለፍ ቃሎች ከፈረንጆቹ 2012 ጀምሮ የተከፈቱ ናቸውም ብሏል።

ፌስቡክ ይህን ተከትሎ ሁሉንም የይለፍ ቃሎች በአንድ ቋት ውስጥ ለማስቀመጥ እየሰራሁ ነው በማለት ለማስተባበል ሞክሯል።

ክሬብስ ከፌስቡክ ሰራተኛ አገኘሁት ባለው ተጨማሪ መረጃ መሰረት፤ እንደዚህ አይነት ችግሮች ያጋጠሙት መተግበሪያውን የሚያበለጽጉት ሰዎች መጀመሪያውኑ የይለፍ ቃሉ ወደ ሚስጥራዊ ኮድ እንዳይቀየር አድርገው ስለሚያዘጋጁት ነው ብሏል።

የፌስቡክ ኢንጂኔር ሰኮት ሬንፍሮ እንደሚሉት ችግሮቹ ምን እንደሆኑ ለመለየት ጥረት አድርገናል መፍትሄውንም እናመጣለን ብለዋል።

መረጃው እንደሚያሳው አብዛኛዎቹ የዚህ ችግር ተጋላጮች የፌስቡክ ላይት ተጠቃሚዎች ናቸው። ኩባንያው ለሮይተርስ በሰጠው ቃል መሰረት "በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ የፌስቡክ ላይት ተጠቃሚዎች፣ በአስር ሚሊዮን የሚቆጠሩ የሌላ ፌስቡክ ተጠቃሚዎችና በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የኢንስታግራም ተጠቃሚዎች የችግሩ ተጋላጮች ናቸው።"

ቢሆንም ግን ቀጥሎ ሊመጣ የሚችለው መፍትሄ የይለፍ ቃልን እንደገና መቀየር ሊሆን ይችላል ተብሏል።

የፌስቡክ መግቢያ (Log in) ደህንነቱ የተጠበቀ አይደለም በማለት ባለፉት ጊዜያት የተለያዩ የዜና ምንጮች ሲተቹት ቆይተዋል። መስከረም ወር ላይ የ50 ሚሊዮን ፌስቡክ ተጠቃሚዎች መረጃ ተጋላጭ ሆኖ እንደነበርም ይታወሳል።

በ2018 መጀመሪያ አካባቢም በሚሊዮን የሚቆጠሩ የፌስ ቡክ ተጠቃሚዎች መረጃ በካምብሪጅ የመረጃ ሳይንስ ኩባንያ እየተጠና መሆኑንም ፌስቡክ ገልጾ ነበር። (ምንጭ፡-ቢቢሲ)