በቀላሉ ሊገመት የሚችል የይለፍ ቃል ለኮምፒውተር ወንጀሎች ያጋልጣል- ጥናት

አብዛኛው የአለማችን የኢንተርኔት ተጠቃሚ በቀላሉ ሊገመት የሚችል የይለፍ ቃል /ፓስወርድ/ ያለው በመሆኑ ለተለያዩ የኮምፒውተር ወንጀሎች ተጋላጭ እየሆነ መምጣቱን አንድ ጥናት አመለከተ፡፡

የብሪታኒያ የሳይበር ደህንነት ማዕከል በእንግሊዝ ዜጎች የኢንተርኔት አጠቃቀም ጥናት በማድረግ በቀላሉ የሚገመቱ የይለፍ ቃላቶችን ይፋ አድርጓል፡፡

በጥናቱም አብዛኛው የአለማችን የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች በቀላሉ ሊገመት የሚችል የይለፍ ቃል ያላቸው በመሆኑ ለተለያዩ የኮምፒውተር ወንጀሎች ተጋላጭ እየሆኑ መምጣታቸውን ተገልጿል፡፡

በብሪታኒያ 42 በመቶ የኢንተርኔት ተጠቃሚ በኦንላይን የመረጃ ቀበኞች በሚፈፀም ወንጀል ገንዘባቸው ይሰረቃል ተብሏል፡፡

ይህ የሚሆነውም የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች በቀላሉ የማይገመት ጠንካራ የይለፍ ቃል ተጠቅመው እራሳቸውን ከጎጂ የኢንተርኔት ድርጊቶች መከላከል ባለመቻላቸው እንደሆነ ተነግሯል፡፡

በጥናቱም በአለማችን አብዛኛው ሰው የሚጠቀማቸውና በቀላሉ የሚገመቱ የይለፍ ቃሎችና ቁጥሮች ይፋ ተደርጓል፡፡

ለአብነትም “12345”፣ “123456789” እና “qwerty” የሚባሉ ቃላቶች ወይም ቁጥሮች በቀላሉ ሚስጥራዊ መረጃዎችን ለመስረቅ በዓለም አቀፍ ደረጃ በጣም የተለመዱ የይለፍ ቃላቶች እንደሆኑ ተጠቁሟል፡፡

“Password”፣ “1111111”፣ የታዋቂ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦችና የዝነኛ ሰዎች መጠሪያና ሌሎች ታዋቂ ስሞች ለይለፍ ቃል መጠቀም በቀላሉ ለኮምፒውተር ወንጀል ድርጊት ተጋላጭ የሚያደርጉ መሆኑን በጥናቱ ተመልክቷል፡፡

(ምንጭ፦ ኢንዲፔንደንት)