ፌስቡክ “አደገኛ ግለሰቦች” ያላቸውን የታዋቂ ሰዎች ገጽ ማገድ መጀመሩን አስታወቀ

ፌስቡክ “አደገኛ ግለሰቦች" ያላቸውን በርካታ የታዋቂ ሰዎች ገጽ ማገድ መጀመሩን አስታወቀ፡፡

ኩባንያው የማህበራዊ ሚዲያው የሴራ (ኮንስፓይረሲ) ድረ-ገጽ የሆነውን 'ኢንፎዋርስ' አቅራቢ አሌክስ ጆንስ፣ የእንግሊዙ ድረ-ገጽ አርታኢ ፖል ጆሴፍ እና የቀድሞው 'የበሬይትባርት' አርታኢ ሚሎ ይአኖፓውሎስን በጥላቻ ንግግር ከሷቸዋል።

የጸረ አይሁድ መልዕክቶችን ያስተላለፈውና 'የኔሽን ኦፍ ኢስላም' መሪ የሆነው ሉዊስ ፋራካሃንም ከታገዱት መካከል ነው ተብሏል።

በእንግሊዝ እንደሚገኘው ብሪቴይን ፈርስት አይነት ጸረ እስልምና ቡድኖችንም ፌስቡክ ማገዱ ተገልጿል።

የአሁኑ እርምጃ በፌስቡክ በሚተዳደረው ኢንስታግራም በተባለው ገጽም ተግራዊ ተደርጓል ነው የተባለው።

"በየትኛውም ርዕዮተ ዓለም ውስጥ ይሁን ግለሰቦችም ሆነ ቡድኖች ጥቃትንና ጥላቻን የሚሰብኩ ወይንም የሚደግፉ ከሆነ ሁሌም እናግዳቸዋልን" ሲል ኩባንያው በመግለጫው አስታውቋል።

"ይህንን የሚጥሱትን ለመለየት የሚደረገው ፍተሻ በጥልቀት የሚካሄድ ሲሆን፣ በዚህ መሠረት ነው እገዳው የተከናወነው" ብሏል።

እገዳ ከተጣለባቸው መካከል የነጭን የበላይነት የሚያቀነቅነው ፖል ኔህለን እና ጸረ-እስልምና አስተሳሰቦችን በማራመድ ከፍተኛ ተከታይ ያላት ላውራ ሉመር ይገኙበታል።

ሉመር ከወራት በፊት ኒውዮርክ በሚገኘው የትዊተር መሥሪያ ቤት እጆቿን በካቴና አስራ በመገኘት ከማህበራዊ ሚዲያው መታገዷን ተቃውማለች።

ሆኖም ፌስቡክ እርምጃ ከመውሰዱ በፊት ማስጠንቀቂያ መስጠቱ ግለሰቦቹም ሆነ ቡድኖቹ ተከታዮቻቸው በሌላ ማህበራዊ ሚዲያ እንዲያገኟቸው ዕድል ይሰጣል በሚል ቅሬታ ቀርቦበታል።

(ምንጭ፡- ቢቢሲ)