ፌስቡክ የጀርመንን የጥላቻ ንግግር ህግ በመጣሱ በ2.3 ሚሊየን ዶላር ተቀጣ

የጀርመን ባለስልጣናት የማህበራዊ ትስስር ድረ ገጽ የሆነው ፌስቡክ የሀገሪቱን የጥላቻ ንግግር ህግ በመጣሱ በ2 ነጥብ 3 ሚሊየን የአሜሪካ እንዲቀጣ ውሳኔ ማሳለፋቸውን አስታውቀዋል።

ባለስልጣናቱ በፌስቡክ ላይ ቅጣቱን በትናንትናው እለት ያሳለፉ ሲሆን፥ ቅጣቱ የተላለፈውም ህጉን የጣሱ ይዘቶችን በፌስቡክ ገፅ ላይ ሲሰራጩ ምንም አይነት የማስተካከያ እርምጃ ባለመውሰዱ ነው ተብሏል።

የጀርመን የፌደራል ፍትህ ቢሮ ባወጣው መግለጫ፥ ፌስቡክ የጥላቻ ንግግር ህግ የጣሱ ይዘቶች እና ህዝቡን የሚረብሹ ምስሎች ሲለቀቁ እርምጃ ባለመውሰዱ ውሳኔው እንደተላለፈበት አስታውቋል።

ፌስቡክ ህገ ወጥ የተባሉ ይዘቶች ላይ የወሰደውን እርምጃም ግልጽ አድርጎ በሪፖርት እንዳላቀረበም ነው ቢሮው ያስታወቀው።

በጀርመን ህግ መሰረት ፌስቡክን ጨምሮ ሁሉም የማህበራዊ ትስስር ድረ ገፆች በበድረ ገፆቻቸው ላይ የሚያጋጥሙ ህገ ወጥ ይዘቶች ላይ የሚወስዷቸውን እርምጃዎች በየስድስት ወሩ በሪፖርት ማሳወቅ እንዳለባቸው ተደንግጓል።

ፌስቡክን ለቅጣት ከዳረጉት ምክንያቶች ውስጥም አንዱ የተሟላ ሪፖርት አለማቅረቡ አንደሆነም ነው እየተነገረ ያለው።

የፌስቡክ ኩባንያ ግን በተላለፈበት የቅጣት ውሳኔ ላይ እስካሁን ምላሽ እንዳልሰጠ እና የይግባኝም አንዳልጠየቀ ነው መረጃዎች የሚያመላክቱት ዘገባዉ የሲኔትዶትኮም ነዉ።