“እንጦጦ ፌሎሺፕ”  በሶፍትዌር ማበልፀግ እና በስራ ፈጠራ ያሰለጠናቸውን ሴቶች አስመረቀ

“እንጦጦ ፌሎሺፕ” ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በሶፍትዌር ማበልፀግ እና በስራ ፈጠራ ያሰለጠናቸውን ሴቶች አስመርቋል፡፡

ተመራቂዎቹ ለሶስት ወራት በሶፍትዌርና ድረ ገፅ ማበልፀግ እና በስራ ፈጠራ የሰለጠኑ ሲሆን ወደ ስራ የሚያስገባቸውን ፕሮጀክትም በምረቃቸው ላይ አስተዋውቀዋል፡፡

የአውቶብስ ትኬት መቁረጫ፣ የታካሚዎች መረጃ መያዣ፣ የጥናት ወረቀቶች መገኛ እና አስጠኚ ማገናኛ ድረ ገፆችም ተመራቂዎቹ ባሉበት (ኦንላይን) የበለፀጉ ናቸው፡፡

ሴቶች በቴክኖሎጂው ዘርፍ ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ መንግስት ድጋፍ ማድረጉን አጠናክሮ ይቀጥላል ያሉት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ ከዚህ በፊት በብሎክ ቼይን ቴክኖሎጂ የሰለጠኑ ሴቶች ከፍተኛ ተከፋይ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

ለጥናትና ምርምር ከሚመደበው በጀት እስከ 25 በመቶ የሚሆነውን ለሴት ተመራማሪዎች እንዲውል ለማድረግ እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡

የካናዳ አምባሳደር አንቶኒ ቼቭረር በበኩላቸው፤ የተመራቂዎቹ ፕሮጀክቶች ወደ ስራ እንዲገቡ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ካናዳ ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል፡፡

የእንጦጦ ፌሎሺፕ መስራችና ስራ አስኪያጅ ወጣት ወንጌላዊት ተካ ሴቶች በቴክኖሎጂው ዘርፍ ውጤታማ መሆን እንደሚችሉ ተመራቂዎቹ የሰሯቸው ስራዎች ማሳያ ናቸው ብላለች፡፡

ተመራቂዎቹ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተውጣጡ መሆናቸውን ከኢኖቬሽንና ቴክሎሎጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡