በተያዘው በጀት ዓመት 278 አገልግሎቶች በኦንላይን ሊሰጡ ነው – የኢኖቪሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር

እስከ 2012 መጨረሻ ድረስ 278 አገልግሎቶች በኦንላይን ዲጂታል አገልግሎት እንደሚሰጡ የኢኖቪሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

የኦንላይን ኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት ለመተግበር 34 ተቋማትን በመምረጥ አገልግሎቱን እንዲሰጡ ወደ ተግባር ለማስገባት እየተሰራ መሆኑና ተቋማቱ የሚሰጡትን አገልግሎት ዓይነት በመለየት ወደ ሲስተሙ እንዲገቡ መደረጉን በኢኖቪሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የመንግስት ኤሌክትሮኒክስ አገልግሎቶችና አፕልኬሽኖች ልማትና አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ አሸናፊ ጋዲሳ ለኢቲቪ ተናግረዋል፡፡

የኦንላይን አገልግሎቱ በተመረጡ 19 ተቋማት ላይ ቅድመ ሙከራ የተደረገ ሲሆን፣ በ7 ተቋማት ሙሉ በሙሉ አገልግሎቱ መተግበሩን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

የኦንላይን አገልግሎቱን ሙሉ በሙሉ እየሰጡ ባሉ ተቋማት ዜጎች አገልግሎት ለማግኘት የሚደርስባቸውን እንግልት በመቀነስ ጊዜና ጉልበታቸውን መቆጠብ ተችሏል ብለዋል አቶ አሸናፊ፡፡

በተጨማሪም ዜጎች የፈለጉበት ቦታ ሆነው በቀላሉ አገልግሎት እንዲያገኙ፣ ተቋማትም አገልግሎታቸው በሰፊው ተደራሽ እንዲያደርጉ፣ የሚነሱ ቅሬታዎችም በመቀነስና ምን ዓይነት አገልግሎት መቼ እንደሚሰጥ ለማወቅ ይረዳል ነው የተባለው፡፡

የኦንላይን አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ተገልጋዮች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል ዳይሬክተሩ፡፡

የኢኖሼሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ፕሮጄክት ቀርጾ ኮንትራክተር በመቅጠር በማንዋል ሲሰጡ የነበሩትን አገልግሎቶች በኦንላይን እንዲሰጡ፣ ተቋማት አግልግሎቶቻቸውን በቴክኖሎጂ እንዲደግፉና የኦንላይን ዲጂታል አገልግሎት እንዲሰጡ ድጋፍና ክትትል እያደረገ እንደሚገኝ ተጠቁሟል፡፡